ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው። (ዕብራውያን 5፥14)
ይህ አስደናቂ ምክር ነው። ሳትረዱት እንዳታልፉት። ከዓመታት የኪሳራ ሕይወት ሊታደጋችሁ ይችላል።
በዚህ ጥቅስ መሠረት፣ በመንፈስ በሳል ለመሆን፣ ቃሉን በጥልቀት ለመረዳትና ለማድነቅ ከፈለጋችሁ፣ መንፈሳዊ አእምሮአችሁ እና ግብረ ገባችሁ በእግዚአብሔር የወንጌል ተስፋ ሊለወጥ ይገባል። ይህ የወንጌል ተስፋ አንዳች እንደማይጎድለው፣ የተመጣጠነ እና የከበረ ወተት ነው። ይህንንም ስታደርጉ፣ መልካሙን ከክፉው መለየት ትችላላችሁ።
በሌላ መንገድ ላስቀምጠው። የእግዚአብሔርን ቃል ለመብላት መዘጋጀት ማለት መጀመሪያ የዕውቀት ፈተና ሳይሆን በቅድሚያ የቅድስና ፈተና ነው። የቃሉን ጠንካራ ምግብ ለመብላት ከፈለጋችሁ፣ መልካሙንና ክፉውን የሚለይ አዕምሮ እንዲዳብር መንፈሳዊ የስሜት ህዋሶቻችሁን ማለማመድ አለባችሁ። ይህ የዕውቀት ብቻ ሳይሆን የቅድስና ፈተና ነው።
ይህ አስደንጋጭ እውነት ነው። በዘፍጥረትና በዕብራውያን ውስጥ ያለውን የመልከ ጼዴቅን ማንነት ለመረዳት የከበዳችሁ ምክንያት፦ ልትመለከቱ የማይገባችሁን ፊልሞች እያያችሁ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። የምርጫ አስተምህሮ ሊገባችሁ ያልቻለው፣ አንዳንድ ህገወጥ የንግድ ሥራ ውስጥ ስለተዘፈቃችሁ ሊሆን ይችላል። የክርስቶስን የመስቀል ላይ ስራ ለመረዳት እየከበዳችሁ ያለው ገንዘብን ስለምትወዱና ንፉግ ስለሆናችሁ ሊሆን ይችላል።
ወደ ብስለት እና ጠንካራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምግብን ወደ መመገብ የሚወስደው መንገድ፣ በትምህርት ሰቃይ መሆን ሳይሆን ታዛዥ መሆን ነው። መጠጥ፣ ወሲብና ገንዘብ ላይ ያላችሁ አቋም፣ ኮምፒውተርና ስልክ አጠቃቀማችሁ፣ የምትዝናኑባቸው ቦታዎች፣ ብሎም ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት፣ ጠንካራ ምግብ የመመገብ አቅማችሁን ይወስናሉ። ካነበባችሁት መጽሐፍ እና ከተመረቃችሁበት ትምህርት ቤት ይልቅ እነዚህ ወሳኝ ናቸው። ቅድስናና እግዚአብሔርን መታዘዝ ከጉብዝናና ከፈጣን አዕምሮ ይበልጣሉ።
ይህን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። በተለይ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ ዘመን ለምንኖር ለእኛ፣ ብዙ መማር እና ዶክትሬት ማካበት የብስለት ቁልፍ እንደሆነ እናስባለን። ሆኖም ግን በእግዚአብሔር ነገር ላይ እንጭጭነት ያነቃቸው ብዙ ሊቃውንት አሉ። በአንጻሩ ደግሞ፣ ያለ ምንም ዲግሪና ዶክትሬት ከጠሊቁ የእግዚአብሔር ቃል በደስታ የሚመገቡና የሚታነጹ በመንፈሳዊ ዕድገት የበሰሉ ብዙ ቅዱሳን አሉ።