የይቅርታ ነጻ አውጪ ኃይል | ሰኔ 15

“ኀጢአትሽ ተሰርዮልሻል።” (ሉቃስ 7፥48)

ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት ተቀምጦ እያለ አንዲት ሴት በእንባዋ እግሩን ልታጥብ ወደ ኢየሱስ መጣች። ስምዖን በቦታው ለተገኙት ሁሉ፣ ይህች ሴት ኃጢአተኛ እንደሆነችና ኢየሱስም እንድትነካው ሊፈቅድላት እንደማይገባ በግልምጫ ሲያወራ፣ ኃፍረት እንደተሰማት ምንም ጥርጥር የለውም።

በእርግጥም ኃጢአተኛ ነበረች። እውነተኛ ለሆነ ኃፍረትም ቦታ አለው። ነገር ግን ኃፍረቱ አብሯት ሊከርም አይገባም።

ኢየሱስ፣ “ኀጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት(ሉቃስ 7፥48)። እንግዶቹም ይህን ሰምተው ሲያጉረመርሙ፣ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” በማለት እምነቷን አጠነከረላት (ሉቃስ 7፥50)።

ኢየሱስ፣ ሽባ ሊያደርጓት የሚችሉ የኃፍረት ውጤቶችን እንድትዋጋ የረዳት እንዴት ነው? የተስፋ ቃልን ሰጣት፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል! እምነትሽ አድኖሻል። ነገሽ የሰላም ይሆናል” አላት። ያለፈ ይቅርታው የወደፊት ሰላምን እንደሚያፈራ አወጀ።

ስለዚህ የእርሷ ጉዳይ ከእንግዲህ የተንጠለጠለው በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ በሚኖራት እምነት ነው። ይህም የተመሰረተው በኢየሱስ የይቅርታ ሥራ እና ነጻ በሚያወጣው ቃሉ ላይ ነው። ሁላችንም ብንሆን ተገቢ የሆነውን ኀፍረት ልንዋጋ የሚገባን በዚህ መንገድ ነው። ተገቢ ያልሆነውን ኀፍረትን ሳይሆን፣ በእውነት ሊሰማን ስለሚገባ፣ ነገር ግን ለረዥም ጊዜ አብሮን ከከረመ ሊያሽመደምደን ስለሚችል ኀፍረት ነው። ተገቢ የሆነውንም ኀፍረት በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሥራ ባገኘነው ጸጋ መርታት እንችላለን።

አሳፋሪ ለሆነው ተግባራችን ይቅርታን አግኝተናል። በዚህም ይቅርታ አማካኝነት ያገኘነውን የወደፊት ጸጋ እና ሰላም አምነን በመያዝ፣ ተስፋ አስቆራጭ ኀፍረትን እና አለማመንን መዋጋት አለብን። 

  • “ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።“ (መዝሙር 130፥4)
  • “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት። ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።“ (ኢሳይያስ 55፥​6–7)
  • “ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው።“ (1ኛ ዮሐንስ 1፥9)
  • “በእርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” (ሐዋርያት ሥራ 10፥43)

ሁላችንም ይቅርታ ያስፈልገናል። ለዛሬም፣ ለነገም፣ ሁልጊዜ ያስፈልገናል። ኢየሱስ ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ ይቅርታ ይሰጠን ዘንድ ሞቷል። ዛሬም ሆነ ነገ እውነታው ይህ ነው፦ የእግዚአብሔር ይቅርታ ለዘለዓለም ነፃ ያወጣናል። ከሚያሽመደምድ ኀፍረት ነፃ ያወጣናል። ይቅርታ በወደፊት ጸጋ የተሞላ ነው።

በእግዚአብሔር ይቅርታ ላይ ተመሥርተን ወደፊት በሚገለጠው ጸጋ ላይ በእምነት ስንኖር፣ አብረውን ሊከርሙና ሊያሽመደምዱን ከሚችሉ የኃፍረት ውጤቶች ነፃ እንወጣለን። በኀጢአታችን ምክንያት ተገቢ የሆነ ኀፍረት ሊሰማን ይገባል። ከዚህም ኀፍረት ሳይቀር፣ እግዚአብሔር በልጁ የመስቀል ላይ ስራ አማካኝነት ነጻ አውጥቶናል። በእርግጥም ይቅርታ ማለት ይህ ነው።