ከብርሃኑ ጀርባ ያለው ብርሃን | ግንቦት 19

እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። (ቈላስይስ 3፥1-2)

ኢየሱስ ዕረፍት ነው። ስለዚህ፣ በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ። ኢየሱስን በጥቃቅን ነገሮች አትተኩት። ከኢየሱስ ርቆ፣ እርሱ ወደሌለበት ምቾት መሮጥ ነፍሳችንን ያደርቃታል።

ጸሎትንና የእግዚአብሔን ቃል ችላ ማለት መጀመሪያ ሰሞን ላይ ነፃነት ሊመስል ይችላል። ከዚያ ግን ትልቅ ዋጋን ያስከፍለናል። ኃይልን እናጣለን። ለኅጢአት የተጋለጥን እንሆናለን። በማይጠቅሙ ጥቃቅን ነገሮች እንያዛለን። ግንኙነቶቻችን የውሸት ይሆናሉ። ኑሯችን ሁሉ ከላይ ከላይ ይሆናል። በሚያስፈራ ደረጃ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች እና ለአምልኮ ፍላጎትን እናጣለን።

በጋ ወይም ምቹ ጊዜ መምጣቱ ነፍሳችሁን እንዲያጨራምታት አትፍቀዱለት። እግዚአብሔር በጋን የሠራው መንግሥተ ሰማይን እንዲተካልን ሳይሆን ቅምሻ እንዲሆነን ነው።

አንድ የፖስታ መልክተኛ ከእጮኛችሁ ደብዳቤ ይዞላችሁ ቢመጣ፣ ከዚያ መልክተኛ ጋር በፍቅር አትውደቁ። ፊት ለፊት ከሚታየው ነገር ጋር በፍቅር ወድቃችሁ፣ በኋላ ለሚመጣው ለዋናው፣ ደብዳቤውን ለላከው ወዳጃችሁ ልባችሁ እንዳይዝል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ያሉ አስደሳች ነገሮች ሁሉ ማዕከል ነው። የሚጠቁሙት ወደ እርሱ ነው። መዝናናትን፣ ምግብ ማብሰልን፣ በአትክልት ስፍራዎች ውስጥ መራመድን ጨምሮ፣ እርሱ የሁሉ ነገር የበላይ ነው (ቈላስይስ 1፥18)። በዚህ ወቅት እንዲህ ሲል ይጋብዘናል፦ “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፥28)።

ጥያቄው፦ “ይህንን ከልብ እንፈልገዋለን ወይ?” የሚል ነው። ክርስቶስ ራሱን የሚሰጠን እኛ በምንፈልገው መጠን ልክ ነው። “እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ” (ኤርምያስ 29፥13)።

ጴጥሮስ ስለዚህ የሚለን ይህን ነው፦ “እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን፣ እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል” (ሐዋርያት ሥራ 3፥19-20)። ንሰሓ ከኅጢአት ዘወር ማለት ብቻ ሳይሆን፣ በተከፈተ እና ታዛዥ በሆነ ቀና ልብ ወደ ጌታ መመለስ ማለት ጭምር ነው።

“ይህ እንዴት ያለ አስተሳሰብ ነው?” ብላችሁ የጠየቃችሁ እንደሆነ፣ በቈላስይስ 3፥1-2 ላይ ታገኙታላችሁ፦ “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን።”

ይህች ምድር የእግዚአብሔር ናት። “የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለሆነ፣ ከተማዋ ፀሓይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም” የተባለላት፣ የሚመጣው ዘላለማዊ የበጋ እና የእረፍት ዘመን ምን እንደሚመስል የምታሳይ፣ ቅድመ ቅምሻ ናት (ራዕይ 21፥23)።

የበጋው ፀሐይ፣ የሚመጣው የእግዚአብሔርን ክብር ብርሃን ማሳያ ነው። በጋ የኖረው ይህንን ለማየት እና ለማሳየት ነው። ይህንን ለማየት ዓይኖቻችሁ እንዲበሩ ትፈልጋላችሁ? ጌታ ሆይ፣ ከብርሃኑ ጀርባ ያለውን ብርሃን አሳየን።