“እነሆ የመረጥሁት፣ የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም። ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” (ማቴዎስ 12፥18-21፤ ከኢሳይያስ 42 የተጠቀሰ)
የእግዚአብሔር አብ ልብ በልጁ የአገልጋይነት ትሕትና እና ርኅራኄ እጅግ ደስተኛ ነው።
ሸምበቆው ጎብጦ ሊሰበር ሲል፣ እስኪፈወስ ድረስ አገልጋዩ በጥንቃቄ አቃንቶ ያቆመዋል። ጧፉም ደግሞ ብርሃን ሳይኖረው ሊጠፋ እየጨሰ እያለ፣ አገልጋዩ ጭፍልቅ አድርጎ አያጠፋውም። ነገር ግን በእጁ ይሸፍነውና በቀስታ በድጋሚ እንዲቀጣጠል ያደርገዋል።
ስለዚህ አብ “እነሆ ልቤ ደስ የሚሰኝበት ባሪያዬ!” ይላል። የልጁ ውበት እና ዋጋ የሚመጣው ከግርማው እና ከየዋህነቱ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሁለቱ ፍጹም በሆነ መጠን ከመዛመዳቸው ነው።
በራዕይ 5፥2 ላይ መልአኩ በታላቅ ድምጽ፣ “ማኅተሞቹን ለመፍታትና መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቶአል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” የሚለው መልስ ይመጣል (ራዕይ 5፥5)።
እግዚአብሔር የይሁዳውን አንበሳ ብርታት ይወደዋል። በእግዚአብሔር ዐይን ማህተሙን ሊፈታ እና የመጨረሻዎቹን ቀናት ሊገልጥ የተገባው እርሱ የሆነው ለዚህ ነው።
ነገር ግን ምስሉ ሙሉ አይደለም። አንበሳው እንዴት ነው ድል ያደረገው? የሚቀጥለው ቁጥር ገጽታውን ያሳያል “ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ” (ራዕይ 5፥6)። ኢየሱስ የአብ ደስታ የሆነው የይሁዳ አንበሳ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የታረደው በግ በመሆኑም ጭምር ነው። ይህ ልዩ የሆነው በስጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክብር ነው። የግርማው እና የየዋህነቱ አስደናቂ መዛመድ ነው።