ለረጅም ጊዜ የተጠበቀው ጉብኝት | ታሕሳስ 7

የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው።

የሉቃስ ወንጌል 1፥68-71

በሉቃስ ወንጌል 1፥68-71 ከኤልሳቤጥ ባል ከዘካሪያስ አፍ ከወጡት ቃላት ሁለት አስገራሚ ነገሮችን ተመልከቱ።

በመጀመሪያ፣ ከዘጠኝ ወር በፊት፣ ዘካርያስ ሚስቱ ልጅ እንደምትወልድ አላመነም ነበር። አሁን ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በጣም ከመመካቱ የተነሣ የመሲሑን መምጣት እንደተፈጸመ በመቁጠር በአላፊ ጊዜ አስቀምጦ ታነባላችሁ፦ “ጎብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና” (“መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቶአልና” አ.መ.ት)። በአማኝ አእምሮ ውስጥ ቃል የተገባ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እንደተፈጸመ ይቆጠራል። ዘካርያስ እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ እንደሆነ ተምሯልና አስደናቂ የሆነ እርግጠኝነት በእግዚአብሔር ላይ አለው፤ እግዚአብሔር “መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷል!” (ሉቃስ ወንጌል 1፥68)።

ሁለተኛ፣ የመሲሑ ኢየሱስ ወደ ምድር መምጣት አምላካችን እግዚአብሔር ምድራችንን መጎብኘቱን ያሳያል። የእስራኤል አምላክ ጎብኝቶ ተቤዥቷል፣ አድኗል። ለብዙ ምዕተ ዓመታት የአይሁድ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደጣላቸው በማሰብ ሲባዝኑ ነበር፤ የትንቢት መንፈስ ቆሞ ነበር፤ እስራኤልም በሮም ግዛት ሥር ወድቃ ነበር። በእስራኤል የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ የአምላካቸውን ጉብኝት ሲጠባበቁ ነበር። ሉቃስ ስለ ሌላ ስምዖን ስለተባለ ታማኝ ሽማግሌም ይነግረናል። ስምዖን “የእስራኤልን መፅናናት ይጠባበቅ ነበር” (ሉቃስ 2፥25)። በተመሳሳይ መልኩም፤ የጸሎት ሰው የነበረችው ሐና የኢየሩሳሌምን መቤዠት ትጠባበቅ ነበር (ሉቃስ 2፥38)።

እነዚህ ቀናት ከፍተኛ የመጠባበቅ እና የጉጉት ቀናት ነበሩ። አሁን ሲጠበቅ የነበረው የእግዚአብሔር ጉብኝት የሚፈጸምበት ጊዜ ደርሷል፤ በርግጥም ማንም ባልገመተው እና ባልጠበቀው መንገድ ሊመጣ ተቃርቧል።