የሕይወቴ ዋነኛ የተስፋ ቃል

የሕይወቴ ዋነኛ የተስፋ ቃል፦ እግዚአብሔር እንዴት ተስፋዬን እንዳጸናው

አንዳንድ ቃላት ነፍሳችሁን ሰርስረው በመግባት አስተሳሰባችሁን በተስፋ መሙላት እና ስለ ሁሉም ነገሮች ያላችሁን አስተሳሳብ መቀየር ይችላሉ። በሮሜ 8፥32 ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መንግሥተ ሰማይ የተናገረውን ስሰማ፣ ለእኔ የሆነውም እንዲሁ ነው። በወቅቱ 23 ዐመቴ ነበር።

ይህንን ጥቅስ ከዚህ በፊት ከነበረኝ አረዳድ በተለየ መልኩ ስመለከተው፣ እግዚአብሔር በልቤ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ የምጠቀምበት ተስፋ ሰጪ እና ሕይወት ቀያሪ ቃል አድርጎ ተክሎታል።

በዙሪያዬ ያሉ ነገሮች ሁሉ ሲናወጡ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ መጽናኛ ቃላት ሁሉ ይህ ለእኔ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖልኛል።

“ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?” (ሮሜ 8፥32)

የመንግሥተ ሰማይ አመክንዮ

ሮሜ 8፥32 የመጽሐፉ የመጀመሪያ 8 ምዕራፎች ክርክር ዋነኛ ማጠቃለያ ነው። ከመልእክቶች ሁሉ ታላቅ የሆነውን የዚህን መጽሐፍ ይህን መልእክት “የመንግሥተ ሰማይ አመክንዮ” እለዋለሁ።

ይህ አመክንዮ በላቲን ቋንቋ ‘ፎርቲኦሪ’ ይባላል፤ ሐሳቡ ሲብራራም ከባድ ነገር ለማድረግ አቅም ካለን፣ ቀላሉን ነገር ማድረግ አያቅተንም በሚል ይገለፃል። ለምሳሌ፣ ልጃችሁ ጎረቤት ሄዶ አንድ ዕቃ እንዲያመጣ ስታዙት፣ እንዴት ዕቃውን እንደሚሰጡኝ እርግጠኛ መሆን እችላለሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ ይህን ‘ፎርቲኦሪ አመክንዮ’ ትጠቀማላችሁ፤ ልጃችሁንም ጎረቤታችን ትላንት መኪናውን ሊሰጠን ፈቃደኛ ነበር፤ ስለዚህ ዛሬ ይህንን ትንሽ ዕቃ ለመስጠት አይቸገርም ትሉታላችሁ።

ጳውሎስ እና ‘ፎርቲኦሪ’

ጳውሎስ ይህንን አመክንዮ በዓለም ታሪክ ታላቁን ክስተት ለማስረዳት ይጠቀምበታል። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለእኛ አሳልፎ ሰጠ እንጂ አልሰሰተውም። ከባዱ ነገር ይህ ነበር። ስለዚህ ሁሉን ደግሞ ለእኛ አሳልፎ ይሰጠናል። ይህ ቀላሉ ነገር ነው። ይህ አመክንዮ በእውነት ሲገባን ሁሉን አቀፍ እና በተስፋ የተሞላ እውነት ይሆንብናል። ይህን ቃል ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ፤ ነገር ግን በ23 ዐመቴ ይህ በእግዚአብሔር የተገለጠ፣ ቅዱስ፣ ሰማያዊ እና የከበረ ቃል ወደ ልቤ ገብቶ የማይነቃነቅ የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል። ይህ ለምን እንደሆነ አብራራለሁ፤ በቅድሚያ ግን በጥቅሱ ሁለት ክፍሎች ላይ እናተኩር።

የጳውሎስ ድንቅ ‘ፎርቲኦሪ’

ጳውሎስ በዚህ ቦታ በዓለም ታሪክ ውስጥ ለታላቁ ክስተት እንዲህ ያለውን ክርክር ሲጠቀም ተመልከት። እግዚአብሔር ለገዛ ልጁ አልራራለትም፤ ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ ሰጥቶታል። ይህ በጣም ከባዱ ነገር ነው። ስለዚህም እርሱ ከራሱ ጋር ሁሉንም ነገር በርግጥ ይሰጠናል። ይህ ቀላሉ ነገር ነው። ይህ ሙግት በተጠራጣሪ አእምሮ ውስጥ ዘልቆ ሲገባ፣ በክብር የተሞላ እና ዘላቂ ተስፋ ይሆናል።

በሕይወቴ ከዛች ቀን በፊት ያንን ጥቅስ ደጋግሜ አንብቤ ነበር። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ይህ አመክንዮ (በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተፈጠረ አመክንዮ) ማለትም ቅዱስ፣ ሰማያዊ፣ ክብር ያለው ይሄ አመክንዮ ወደ ነፍሴ ውስጥ ዘልቆ ገባ፤ ተተከለም። የማይናወጥ መሠረት፣ ሕያው የተስፋ እና የኃይል ምንጭ ሆነኝ። ምክንያቱን ቀጥዬ እገልጻለሁ። ግን ከዚያ በፊት በዚህ ጥቅስ ሁለት ክፍሎች ይዘት ላይ ለአንድ አፍታ ከእኔ ጋር አተኩር።

ለዘላለም ደስታ ታላቁ እንቅፋት

በቅድሚያ ስለ ሮሜ 8፥32 የመጀመሪያ ክፍል እናሰላስል። “ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ…”

ለዘላለም ደስታችን እንቅፋት የሆኑት ምንድን ናቸው? አንዱ ኅጢአት ነው። ሁላችንም ኅጢአተኞች ነን (ሮሜ 3፥23)፤ የኅጢአት ደሞዝ ደግሞ ሞት ነው (ሮሜ 6፥23)። ሌላኛው እንቅፋት የእግዚአብሔር ቁጣ ነው። እግዚአብሔር በኅጢአታችን ምክንያት ሁሌም በእኛ ላይ የሚቆጣ ከሆነ ዘላለማዊ ደስታ ሊኖረን አይችልም። ጳውሎስም በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር መሆናችንን በግልጽ ይናገራል፦ “እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን” (ኤፌሶን 2፥3)።

እኔ ግን አንድ ተጨማሪ እና ዋነኛ እንቅፋት ያለ ይመስለኛል። ጳውሎስም በጥቅሱ የመጀመሪያ ክፍል ይናገረዋል (ሮሜ 8፥32)፤ እርሱም እግዚአብሔር ለልጁ ያለው የማያልቅ ፍቅር ነው። እግዚአብሔር አሳልፎ የሰጠን የሚወደውን የራሱን ልጅ ነው፤ ይህ ለእርሱ እጅግ ከባድ እንደነበረ መገመት አያቅተንም።

እግዚአብሔር የራሱን ልጅ አሳልፎ መስጠት ይችላልን?

ጳውሎስ ኢየሱስን የእግዚአብሔር የገዛ ልጅ ብሎ ሲጠራው እንደ እርሱ ያሉ ሌሎች እንደሌሉና ምን ያህል ለአባቱ ውድ እንደሆነ ለመግለጽ ነው። ኢየሱስ በምድር ሳለ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ “ይህ የምወደው ልጄ ነው” ብሎ ተናግሯል (ማቴዎስ 3፥17 ፤ 17፥5)። ኢየሱስ ራሱ በገበሬዎቹ ምሳሌ ላይ ሲናገር  “አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወድደው ልጁ ነበረ” ብሏል (ማርቆስ 12፥6)። የሮሜ 8፥32 ዋነኛ ሐሳብ እግዚአብሔር ለልጁ ያለው ፍቅር በእርሱ እና በድህነታችን መካከል ምን ያህል ታላቅ የሆነ እንቅፋት እንደነበር ማሳየት ነው። እግዚአብሔር በእውነት ልጁ እንዲሰደብ፣ እንዲተፋበት፣ እንዲገረፍ፣ በመስቀል ላይ እንዲሰቀል፣ በጦር እንዲወጋ አሳልፎ ይሰጠዋልን?

እግዚአብሔር ለልጁ አልራራለትም

እግዚአብሔር በእውነት ልጁን አሳልፎ ከሰጠ፣ የወደፊት ዕቅዱ ፈጽሞ እንደማይበላሽ እርግጠኛ መሆን አለበት ማለት ነው። ሮሜ 8፥32 እንደሚነግረን እግዚአብሔር እውነትም ልጁን አሳልፎ ሰጠው። ‘ይሁዳ አይደለም እንዴ አሳልፎ የሰጠው?’ ልትሉ ትችላላችሁ (ማርቆስ 3፥19)፤ ‘ጲላጦስ አይደለም እንዴ አሳልፎ የሰጠው?’ ልትሉ ትችላላችሁ (ማርቆስ 15፥15) ፤ ‘ሄሮድስ እና ሕዝቡ አይደሉም እንዴ አሳልፈው የሰጡት?’ ልትሉ ትችላላችሁ (ሐዋርያት ሥራ 4፥27-28)፤ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ‘እኛ ራሳችን አሳልፈን አልሰጠነውም እንዴ?’ ልትሉ ትችላላችሁ (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥3፤ ገላትያ 1፥4፤ ጴጥሮስ 2፥24)፤ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ‘ኢየሱስ ራሱን አሳልፎ አልሰጠምን?’ (ዮሐንስ 10፥17 ፤ 19፥30) የሚለው ሲሆን፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ መልሱ ‘አዎ’ ነው።

ቢሆንም ግን በሮሜ 8፥32 ጳውሎስ እያለን ያለው ከእነዚህ ሁሉ ውሳኔዎች ጀርባ፣ እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ሰዎች ተጠቅሞ ልጁን ለሞት አሳልፎ እንደሰጠ ነው። “እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ” (ሐዋርያት ሥራ 2፥23)። ይሁዳ፣ ጲላጦስ፣ ሄሮድስ እና ሌሎቹንም ተጠቅሞ እግዚአብሔር ልጁን አሳልፎ ሰጠ። ከዚህ የከበደ ነገር ሆኖም አያውቅም፤ ወደፊትም አይሆንም።

የአመክንዮው ቀላ ክፍል

ስለዚህ በጳውሎስ “ፎርቲኦሪ” አስተሳሰብ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ደስታን እውን ለማድረግ ከባዱን ነገር አድርጓል። የገዛ ልጁን አሳልፎ ሰጥቶናል። ይህ ታዲያ የሚያረጋግጠው ምንን ነው? ጳውሎስ ጥያቄውን በጥያቄ ይመልስልናል፦ “ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?” ጳውሎስ ከአንባቢው የሚጠብቀው እርግጠኝነትን ሲሆን እርሱም “እንዴታ! በርግጥ ከእርሱ ጋር ሁሉንም ነገር በቸርነቱ ይሰጠናል” የሚል ነው።

ሙሉውን ጥቅስ ስንመለከት “ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?”

“ሁሉንስ ነገር!” ይህ ማለት ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት ቃል ተገብቶልናል ማለት አይደለም። ጳውሎስ አራት ቁጥሮች ዝቅ ብሎ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን” ብሎ ጽፏል (ሮሜ 8፥36)።

ሁሉንም ነገር ይሰጠናል ማለት የእርሱን ፈቃድ ለማስፈፀም፣ እርሱን ለማክበር፣ ለመዳን፣ ለዘላለማዊ ደስታ የሚያስፈልጉንን ሁሉንም ነገሮች ይሰጠናል ለማለት ነው (ሮሜ 8፥30)።

  • ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን (ቁ. 28)
  • የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው (ቁ. 29)
  • ያጸደቃቸውን አከበራቸው (ቁ. 30)
  • ማን ሊቃወመን ይችላል? (ቁ. 31)
  • የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? (ቁ. 33)
  • ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? (ቁ. 35)
  • ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን (ቁ. 35-37)
  • ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም (ቁ. 38-39)

ተስፋዬ በሮሜ 8፥32 ላይ የተንጠለጠለ ነው

አሁን ወደ መጀመሪያው እንመለስ። በ23 ዐመቴ ይህ ቃል ወደ ልቤ ገብቶ ነገሮችን የማይበትን አተያይ ሁሉ እንደቀየረ እና ሙሉ ተስፋ እንደሰጠኝ ተናግሬ ነበር። ምን ማለቴ ነው? ይህ ሰማያዊ አመክንዮ እግዚአብሔር ልጁን ሳይራራ አሳልፎ መስጠቱ እስከዛሬ የማምንበትን ወይም ወደፊት የማምነውን የተስፋ ቃል ሁሉ ያረጋግጥልኛል ማለቴ ነው። በእያንዳንዱ ቀን ሕይወቴን የምኖረው በእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ምሪት ነው። ሁሉንም የማረጋግጠው ሮሜ 8፥32 ነው። ይህ እንዴት አስፈላጊ እንደሆነ አያችሁ?

ጳውሎስ “በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና” ይላል (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)። ይህ የሆነው አብ ልጁን አሳልፎ ለመስጠት ስላልራራ ነው። ከፍርሀት፣ ስግብግብነት፣ ንዴት፣ ኩራት ወዘተ ጋር የማደርገው ተጋድሎ ሁሉ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የሚመራ ነው ማለት ነው። ልክ እንዲሁ ለቅድስና፣ ለትሕትና፣ ለሰላም እና ለፍቅር የማደርገውም ተጋድሎ በእግዚአብሔር ቃል የተስፋ ቃሎች ላይ የሚደረጉ ትግሎች ናቸው።

ከእነዚህ ሁሉ ተጋድሎዎች ጀርባ ይህ ሰማያዊ አመክንዮ አለ፦ ‘ልጄን አሳልፌ ለመስጠት አልራራሁም፤ ስለዚህ ለአንተ/አንቺ የገባሁት ቃል ፈጽሞ አይወድቅም። እኔ አግዛችኋለሁ፤ ስለዚህ እንድታደርጉ የጠራኋችሁን አድርጉ።”

ጆን ፓይፐር