እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም። (ዕብራውያን 10፥39)
ፍቅር የሚያስከፍለውን ጊዜያዊ ዋጋ ተመልክታችሁ፣ በእግዚአብሔር ታላቅ ተስፋዎች ከማመን ወደኋላ አትበሉ። የምታፈገፍጉ ከሆነ፣ ተስፋዎቹን ብቻ ሳይሆን የምታጡት እናንተም ትጠፋላችሁ።
ወደ ኋላ መመለስ ወይም መጽናት ቀላል ጉዳዮች አይደሉም። ገሃነም የመግባት እና ያለመግባት ጉዳይ ነው። ባንጸና እንደው ጥቂት ብድራቶችን እናጣለን ማለት አይደለም። ዕብራውያን 10፥39 “እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም” ይላል። መጥፋት ይህ የዘላለም ፍርድ ነው።
ስለዚህ፣ አንዳችን ሌላችንን እናስጠነቅቃለን፦ ርቃችሁ እንዳትጠፉ! ዓለምን አትውደዱ። የሚታጣው ቀላል ነገር ነው ብላችሁ አታስቡ። በእግዚአብሔር ተስፋዎች ከመደሰት ይልቅ በኀጢአት ተስፋዎች ልባችሁ የሚማረክ ከሆነ እጅጉን ፍሩ። ዕብራውያን 3፥13-14 እንደሚለው፣ “ነገር ግን ከመካከላችሁ ማንም በኀጢአት ተታሎ ልቡ እንዳይደነድን፣ “ዛሬ” እየተባለ ሳለ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ። በመጀመሪያ የነበረንን እምነት እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንይዝ ከክርስቶስ ጋር ተካፋዮች እንሆናለን።”
ነገር ግን፣ ከሁሉም በላይ፣ እጅግ ውድ በሆኑት የእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ በማተኮር እና ክርስቶስ በደሙ የገዛልንን ታላቅ ሽልማት ከምንም ነገር በላይ በማስበለጥ እርስ በእርስ መረዳዳት አለብን። በዕብራውያን 10፥35 ላይ “ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ” የሚለውን እርስ በርሳችን ልንባባል ይገባል። ከዚያም አንዳችን ለሌላችን የብድራታቸንን ታላቅ ዋጋ በማሳየት፣ በማበረታታት፣ እና በማስናፈቅ መጽናትን ልንከፋፈል ይገባል።
የስብከትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እና አገልግሎቶች ዋና ዓላማ ይህ ነው፦ ለሰሚዎቻችን ሁሉ ክርስቶስ የገዛቸውን ነገሮች ውድነት በማስገንዘብ ከሁሉ በላይ ከፍ አድርገው ዋጋ እንዲሰጡት መርዳት ነው። ይህም ማለት ሰዎች ሁሉ ይህንን ወደር የሌለውን መስዋዕትነት እንዲያዩትና እንዲያጣጥሙት በማገዝ፣ በእርካታቸው እና በአገልግሎቶቻቸው ውስጥ የእግዚአብሔር ታላቅነት ደምቆ እንዲታይ ማድረግ ነው።