ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥35-38)
እግዚአብሔር ፍጥረትን ሲፈጥር የነበረውን ጥልቅ ተሳትፎ የሚያሳዩ አንዳንድ ክፍሎችን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እያየሁ ነበር።
ለምሳሌ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥38 ላይ፣ አንድ የተዘራ ዘር ሲበቅል የተለየ መልክ እንደሚይዝ ሁሉ፣ የሚመጣውም “አካል” ከሌላው አካል የተለየ መልክ እንዳለው በንጽጽር ጳውሎስ ያሳያል። እንዲህም ይላል፦ “እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል።” (የተጻፈበትን ቋንቋ ከተመለከትን፣ ክፍሉ የሚለው ለእያንዳንዱ የዘር “ዐይነት” አካል ይሰጣል ሳይሆን፣ ለእያንዳንዱ ዘር የራሱን አካል ይሰጠዋል ነው።)
እግዚአብሔር እያንዳንዱ ዘር (ዝርያ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዘር በተናጠል!) የራሱን ልዩ የሆነ ተክል እንዲያወጣ ማድረጉ የእግዚአብሔርን የጠለቀ ተሳትፎ የሚያሳይ አስደናቂ ማብራሪያ ነው። ስለ እያንዳንዱ ዘለላ እና ፍሬ እግዚአብሔር ግድ ይለዋል።
ጳውሎስ እዚህ ላይ ስለ ዝግመተ ለውጥ እያስተማረ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በፍጥረት ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ጣልቃ ገብነት እያሳየን ነው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ እግዚአብሔር ካልሠራው በስተቀር የትኛውም ዐይነት ተፈጥሯዊ ሂደት ሊጸነስ አይችልም ብሎ ጳውሎስ ያምናል።
እንደገና በመዝሙር 94፥9 ላይ፦ “ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?” ይላል። መዝሙረኛው ዳዊት ዐይንን ያበጀውና ጆሮንም በቦታው ተክሎ የመስማት ሥራውን እንዲሰራ ያደረገው እግዚአብሔር መሆኑን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ይጽፋል።
ስለዚህ፣ በሰው ልጅ ዐይን ውስብስብነት ስንገረም እና በጆሮ አሠራር ስንደነቅ፣ የምንደነቀው እና የምንገረመው በድንገተኛ ግጥምጥሞሽ ሳይሆን፤ በእግዚአብሔር አዕምሮ፣ ፈጠራና ኃይል ነው።
በተመሳሳይም በመዝሙረ ዳዊት 95፥5 ላይ፦ “እርሱ ፈጥሮአታልና፣ ባሕር የእርሱ ናት፤ እጁም የብስን አበጀ” ይላል። ባሕር የእርሱ ናት ሲል፣ አሁንም ያለችው ባሕር የእርሱ ናት ማለቱ ነው።
ይህን ሁሉ ሥራ ከቢሊዮን ዓመታት በፊት እርሱ እንዲያው ከውጭ ሆኖ በማዘዝ ብቻ መልክ እንዲይዙ አላደረገም። ይልቁንም በቀጥታ በመሳተፍ እርሱ ራሱ ስለሠራው የግሉ ነው። አንድ ሠዓሊ የሥዕል ሥራው የራሱ እንደሆነው ሁሉ፣ ፍጥረት ሁሉ የእጅ ሥራው ሆኖ የፈጣሪውን ምልክት ተሸክሟል።
እነዚህን ነገሮች የጠቆምኩት በፍጥረት አጀማመር ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ንትርኮች ለመፍታት አይደለም። ይልቅ የፍጥረትን አስደናቂነት በምትመለከቱበትና በምታደንቁበት ጊዜ፣ እግዚአብሔርን እንድታስቡት፣ እንድታከብሩት እና እንድታሰላስሉት ለማስታወስ ነው።