…ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው። (ኤፌሶን 2፥7)
በመጽሐፉ ካሉ የክርስቶስ ዳግም ምፅአት ምስሎች ውስጥ የሉቃስ 12፥35-37 እጅግ አስደናቂው እንደሆነ አስባለሁ። ይህ ክፍል የአንድ ጌታ ከሰርግ ግብዣ መመለስን እንዲህ አድርጎ ምስሉን ያቀርባል፦
“በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችም ምሰሉ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል።” (ሉቃስ 12፥35-37)
በርግጥ አገልጋዮች ተብለናል፤ ስለዚህ የታዘዝነውን በትክክል መፈጸም አለብን። ነገር ግን የዚህ ምስል ወይም የዚህ ታሪክ አስገራሚ ነገር ጌታው ለማገልገል ግድ ማለቱ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ይህን ከርሱ ልንጠብቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም “የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና” ብሏልና (ማርቆስ 10፥45)። ነገር ግን ሉቃስ 12፥35-37 የዳግም ምፅአቱ ምሳሌ ነው፤ የሰው ልጅ በአባቱ ክብር የሚገለጥበት ነው፤ “ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው” (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥7-8)። ኢየሱስ ለምን በዳግም ምፅአቱ ወቅት እንደ አስተናጋጅ ይመሰላል?
ምክንያቱም የክብሩ ዋና ክፍልና መገለጫ፣ ለተጎሳቆሉ ሰዎች በለጋስነት የሚፈሰው የጸጋው ባለጠግነት ነው። ለዚህም ነው በኤፌሶን 2፥7 “በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው” ተብሎ የተጻፈው።
የእግዚአብሔር ታላቅነት ምንድነው? በዚህ ዓለም ላይ ልዩ የሚያደርገው ነገርስ ምንድን ነው? ኢሳይያስ መልስ አለው፦ “ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ እንደ አንተ ያለውን አምላክ ያየ ዐይን፣ ያደመጠ ጆሮ ፈጽሞ አልነበረም” (ኢሳይያስ 64፥4)። እንደዚህ ያለ ሌላ አምላክ የለም። የማያልቅ ባለጠግነቱን ለሚደገፉበትና በእርሱ ደስተኛ ለሚሆኑ ሰዎች መስጠቱን ፈጽሞ አያቋርጥም።