ትንሣኤው ለእኛ ያለው ትርጉም | ሚያዚያ 27

“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። (ሮሜ 10፥9)

“እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን” ማለት ምን ማለት ነው? ሰይጣንም እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳው ያምናል። እንደውም ሲፈጸም አይቷል። ስለዚህ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፣ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ትንሣኤ ምን ትርጉም እንዳለው ልናሰላስል ይገባል።

የትንሳኤ ትርጉም እግዚአብሔር ለእኛ ወግኗል ማለት ነው። በእኛ ደረጃ ዝቅ ለማለት ወስኗል። መረሳታችንን እና መገፋታችንን ሁሉ ሊያስወግድልን ፈቅዷል ማለት ነው።

የኢየሱስ ትንሳኤ፣ በራሳችን መንገድ ወደ ክብር መድረስ እንደማንችል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ያንን ሊያሳካልን እንደቆረጠ ለእስራኤል እና ለዓለም ያበሰረበት የእግዚአብሔር አዋጅ ነው።

ትንሳኤ፣ በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ተካፋዮች እንደሚሆኑ፣ ይህም ኃይል ደግሞ በጽድቅ መንገድና በሞት ጥላ መካከል እንደሚመራቸው ከእግዚአብሔር የተሰጠ ቃል ኪዳን ነው።

ስለዚህ እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን እንዳስነሣው በልብ ማመን፣ እውነታውን ከመቀበለ ያለፈ ነው። ይኸውም እግዚአብሔር ለእናንተ እንደሚወግንና ራሱን ዝቅ አድርጎ ሕይወታችሁን በመለወጥ ለዘላለም ደስታ እንደሚያበቃችሁ መተማመን ማለት ጭምር ነው።

በትንሳኤ ማመን ማለት ስለ ሕይወት፣ ስለ ተስፋ እና ስለ ጽድቅ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ሁሉ ያለማመቻመች ማመን ማለት ነው።

በሌላ አገላልጽ፣ በእግዚአብሔር ኃይልና ፍቅር ከመታመናችን የተነሳ ዓለምን የማጣት ፍርሃት ወይም የዓለምን ጥቅም መጎምጀት፣ ፈቃዱን እንዳንታዘዝ አያደርገንም ማለት ነው።

በቅዱሳን እና በሰይጣን መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው። ልባችን እርሱን ይወድ ዘንድ፣ በልጁም ትንሣኤ ያርፍ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ልባችንን ይግረዝ (ዘዳግም 30፥6)።