የመከራ ትርጉም | ጥቅምት 26

ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና። (ዕብራውያን 11፥26)

መከራን የምንመርጠው እንደው ስለተነገረን ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የነገረን አምላክ የዘላለም ደስታ መንገድ እንደሆነ ስለገለጸልንም ጭምር ነው።  

እግዚአብሔር ወደ መከራ ታዛዥነት የጠራን፣ ለግዳጅ ያለንን ቁርጠኝነት እንድናሳይ፣ የሞራል ቁርጠኝነታችንን ወኔ እንድንገልጥ፣ ወይም ደግሞ ሥቃይ የመቻል አቅማችንን ከፍ ለማድረግ አይደለም። ይልቅ በመከራ ውስጥ የሚያሳልፈን ወደር የሌለውን የክብሩን ታላቅነት እና ውበት ለመግለጥ ሲሆን፣ በዚህም ለልጆቹ ፍጹም እርካታ የሚሰጡትን ተስፋዎቹን አትረፍርፎ ይሰጣል።

ሙሴ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶ፣ “ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ” (ዕብራውያን 11፥25-26)። ስለዚህ ሙሴ በመታዘዙ ምክንያት ሽልማቱ ከፍ ብሎ ሊታይ እና ሊከብር ችሏል። ሽልማቱን ያከበረው መከራ የመቀበል ወኔው ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ለእርሱ በክርስቶስ በኩል የሆነው ሁሉ ነው።

የክርስቲያን ሄዶኒዝም ትርጉም ይህ ነው። በመከራ ውስጥ ያለውን ደስታን ስናሳድድ፣ የደስታችን ምንጭ የሆነውንና ፍጹም እርካታን የሚሰጠውን የኢየሱስ ክርስቶስን ዋጋ ከፍ እናደርጋለን። ድቅድቅ ጭለማ በሆነው የመከራችን ዋሻ መጨረሻ ላይ፣ ራሱን እግዚአብሔርን እንደ ታላቅ ብርሃን እያበራ እናገኘዋለን።

በመከራ ውስጥ የሚገኘው የደስታ ግብና መሠረት ራሱ ኢየሱስ እንደሆነ ዕውቅና ካልሰጠን ግን የመከራችን መሠረታዊ ትርጉም ይጠፋል።

ትርጉሙ ይህ ነው፦ የምናገኘው ትርፍ እግዚአብሔር ነው። የምናገኘው ትርፍ እግዚአብሔር ነው። ትርፉ እግዚአብሔር ራሱ ነው። የመከራችን ትርጉም ይሄ ነው። እግዚአብሔርን እናተርፋለን።

የሰው ልጅ የተፈጠረው እግዚአብሔርን ለማክበር ነው። እኛ በእርሱ ስንረካ፣ እግዚአብሔር በእኛ እጅግ ይከብራል። ይህ እውነት ከየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ይልቅ በመከራ ውስጥ ስናልፍ እውነትነቱ ግልጽ ይሆናል።