የፍጥረት መልእክት | ነሐሴ 24

ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤ የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረት መልክ መስለው ለወጡ (ሮሜ 1፥22-23)።

አንድ ሰው ከሚስቱ አስበልጦ የጋብቻ ቀለበቱን ቢወድ ታላቅ ሞኝነት እና እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው። ነገር ግን ይህ ጥቅስ የሚነግረን እንዲህ ያለ ሞኝነት እንደተከሰተ ነው።

የሰው ልጆች ከዋናው ከእግዚአብሔር ክብር፣ ኀይልና ቀዳሚ ፍቅር ይልቅ፣ ከእርሱ ጋር ከማይወዳደረው ፍጥረቱ ጋር በፍቅር ወድቀዋል። ከእርሱ ይልቅ የእርሱን ልዕልና ለማስተጋባት የተፈጠሩት ፍጥረታት፣ የሰዎችን ቀልብ ስቧል። በዚህም የፍጥረትን ጩኸት መስማት ተስኗቸዋል።

ፍጥረት ሁሉ ጮክ ብሎ የሚያውጀው መልዕክት ይህ ነው፦

ከዚህ ከሚታየው አጽናፈ ዓለም ጀርባ ታላቅ የክብር፣ የኀይል እና የደግነት አምላክ አለ፤ ስለፈጠራችሁ የእርሱ ናችሁ። አመፀኛም ሆናችሁ እንኳ እርሱ ይታገሣችኋል፣ በሕይወትም ያቆያችኋል። ተመለሱ፣ ንስሓ ግቡና ተስፋችሁን በእርሱ ላይ አድርጉ። በእጆቹ ስራ ብቻ ሳይሆን በእርሱም ደስ ይበላችሁ።

መዝሙር 19፥1-2 እንደሚነግረን፣ ቀን እንኳ ሳይቀር ለሚሰሙት ሁሉ ንግግር ያቀርባል። በደማቋ ፀሐይ፣ በሰማያዊው ሰማይ፣ በደመና፣ ሊገለጹ በማይችሉ ቅርጾች እና ቀለማት ወስጥ ውብ በሆነው ቋንቋ አዋጅን ያውጃል። ሌሊትም እንዲሁ ተመሳሳይ የእውቀት መልዕክትን በጨለማው ባዶነት፣ በበጋው ጨረቃ፣ ሊቆጠሩ በማይችሉ ከዋክብት፣ በአስደናቂ ድምጾች፣ በነፋሻማ አየርና እና በሰሜን ብርሃናት ውስጥ ለሚሰማው ሁሉ ይናገራል።

ቀን እና ሌሊት በጋራ አንድ ነገር ይላሉ፦ እግዚአብሔር ክቡር ነው! እግዚአብሔር ክቡር ነው! ዐይናችሁን ከፍጥረት ሁሉ ላይ አንስታችሁ፣ ዋናው ፈጣሪው ላይ አድርጉት! ፍጥረትን የእርካታችሁ መዳረሻ ከማድረግ ተመለሱና የክብር ሁሉ ጌታ በሆነው በእርሱ ደስ ይበላችሁ።