ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ። (ፊልጵስዩስ 3፥1)
እግዚአብሔር በእርሱ በመደሰታችን ምክንያት እንደሚከብር ማንም አስተምሮኝ አያውቅም ነበር፤ ማለትም በእግዚአብሔር መደሰታችን በራሱ፣ ውዳሴያችንን ከግብዝነት አላቆ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆን ያደርገዋል።
ነገር ግን ጆናታን ኤድዋርድስ በግልጽ እና በኃይል እንዲህ ተናግሮታል፦
እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ራሱን በሁለት መንገድ ያከብራል፦ (1) በመረዳታቸው ልክ በመገለጥ፤ (2) ራሱን ለልባቸው በመግለጥ፣ በመገለጦቹ በመደሰታቸው እና በመርካታቸው… ክብሩ በመታየቱ ብቻ ሳይሆን ክብሩ ውስጥ በሚገኘው ደስታም ይከብራል…
ክብሩን ካዩት ሰዎች በላይ፣ ክብሩን አይተው በሚደሰቱት እግዚአብሔር ይበልጥ ይከብራል… ክብሩን ስለ ማየቱ የሚመሰክር አንድ ሰው፣ ክብሩን አይቶ ስለ መደሰቱ እንደሚመሰክረው ሰው እግዚአብሔርን አያከብረውም።
ይህ ለእኔ አስደናቂ ግኝት ነበር። እግዚአብሔርን በመላ ዓለሙ እጅግ ውድ የሆነ እውነት አድርጌ እንዳከብረው፣ በእርሱ መደሰትን መፈለግ አለብኝ። ደስታ ከአምልኮ ጎን ለጎን የቀረበ ምርጫ አይደለም። የአምልኮ አስፈላጊ ክፍል ነው። በርግጥም የአምልኮው ዋናው ክፍል በእግዚአብሔር ክብር መደሰት ነው።
በሚያመሰግኑት ነገር ደስ ሳይሰኙ፣ እግዚአብሔርን ለሚያመሰግኑ ሰዎች ስም አለን። ግብዞች እንላቸዋለን። ኢየሱስ “እናንት ግብዞች፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው’” ብሏል (ማቴዎስ 15፥7–8)። ይህ እውነት ማለትም እውነተኛ ውዳሴ በፍጹም እርካታ መጥለቅለቅ ሲሆን፣ የሰው ልጅም ትልቁ የሕይወት ግቡ ለእግዚአብሔር ክብር ሲል ከዚህ እርካታ ደጋግሞ መጎንጨት ነው፤ ስለዚህ ይህ እውነት ምናልባት እስካሁን ካየኋቸው ሁሉ በላይ ነፃ አውጭ የሆነ ግኝት ነው።