የጋብቻ ምስጢር | ጥቅምት 15

ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ”። ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው፤ እኔም ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን እናገራለሁ።“ (ኤፌሶን 5፥31-32)

ጳውሎስ በዚህ ክፍል እየጠቀሰ ያለው በዘፍጥረት 2፥24 የሚገኘውን እና ኢየሱስ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ተናገረ ያለውን ቃል ነው (ማቴዎስ 19፥5)። ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ይላል። ይህ ቃል ሰው በኅጢአት ከመውደቁ በፊት የተነገረ ሲሆን፣ ክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያንን ያስታውሰናል። ጳውሎስ ይህ ቃል ታላቅ ምስጢር የያዘ መሆኑን ይናገራል።

ይህ የሚነግረን እግዚአብሔር ወንድ እና ሴትን ሲፈጥር እና በጋብቻ ሊያጣምራቸው ሲያስብ እንዲሁ በዘፈቀደ የሆነ ነገር አለመሆኑን ነው። በክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው ግንኙነት ላይ የተመሠረተ የዘላለማዊ ዕቅዱ አካል መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ስለዚህ ጋብቻ ምስጢራዊ ነው፦ በግልጽ ከሚታየው ባለፈ ጥልቅ ትርጉምን የያዘ ነው። እግዚአብሔር ወንድ እና ሴትን ፈጥሮ በጋብቻ ያጣመራቸው በክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በዚህ እንዲገለጥ አስቦ ነው።

ጳውሎስ ከዚህ ምስጢር የሚያሳየን ነገር የባል እና የሚስት ሚናዎች በአቦ ሠጡኝ የተሰየሙ ግብሮች ሳይሆኑ በክርስቶስ እና በቤተ ክርስቲያን ማንነቶች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ነው።

ባለ ትዳር የሆንን ሰዎች እግዚአብሔር እንዴት ይህንን ከራሳችን በላይ የሆነ ምስጢራዊ ግንኙነት እንድንለማመድ እንደፈቀደልን እያሰብን ልንገረም ይገባል።

ጳውሎስ እንደሚናገረው ይህ በክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለ ግንኙነት የጋብቻ መሠረት ነው። የትዳር አጋሮች ደስታቸውን በትዳር ጓደኛቸው መደሰት ውስጥ እንዲፈልጉ መናገር ብቻ በቂ አይደለም። እውነት ነው፤ ነገር ግን በቂ አይደለም። ባሎች እና ሚስቶች በክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነትም እንዲለማመዱ ማሳሰብ ይገባል። ይህም ማለት እግዚአብሔር በክርስቶስ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ ባለው ንጹሕ እና ደስተኛ ዕቅድ መሠረት ሊኖሩ ይገባቸዋል ማለት ነው።

ያገባችሁም ሆነ ያላገባችሁ፣ ወጣቶችም ሁኑ ሽማግሌዎች፣ ይህንን በአንክሮ እንደምትመለከቱ ተስፋ አደርጋለሁ። በቃል ኪዳን ጠባቂው ክርስቶስ እና ቃል ኪዳን ጠባቂዋ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው መገለጥ በዚህ ጥልቅ ሚስጥር ላይ የተመሠረተ ነው።