“ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ።” (1ኛ ሳሙኤል 15፥24)
ሳኦል ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ለመታዘዝ የመረጠው ለምን ነበር? ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ይፈራ ስለነበር ነው። አምላኩን ሳይታዘዝ ከሚመጣበት መዘዝ ይልቅ፣ በመታዘዙ ምክንያት ከሰው የሚመጣበትን መዘዝ ፈራ። ከእግዚአብሔርን መከፋት ይልቅ የህዝቡን መከፋት ፈራ። ይህም ደግሞ ለእግዚአብሔር ትልቅ ስድብ ነው።
እንደውም አንድ ሰው የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ንቆ፣ ሰው ሊያደርገው የሚችለውን መፍራቱ ትዕቢት ነው ይለናል ኢሳይያስ። የእግዚአብሔርን ጥያቄ እንዲህ ሲል ያስተጋባል፦ “የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤ ሟች የሆኑትን ሰዎች፣ እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች ለምን ትፈራለህ? የፈጠረህን፣ ሰማያትን የዘረጋውን፣ ምድርን የመሠረተውን እግዚአብሔርን ረስተሃል” (ኢሳይያስ 51፥12-13)።
ሰውን መፍራት ትዕቢት ላይመስል ይችላል፣ እግዚአብሔር ግን “ትዕቢት ነው!” ይለናል፦ “ሰውን የምትፈራ እኔን ፈጣሪህን ግን የምትረሳ፣ ማነኝ ብለህ ነው የምታስበው?” ሲል ይሞግተናል።
ዋናው ዐሳብ ይህ ነው፦ ሰውን የምትፈሩ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቅድስና፣ እንዲሁም የአብን እና የልጁን ኢየሱስን ክብር መካድ ጀምራችኋል ማለት ነው። እግዚአብሔር ከሰው ይልቅ ፍጹም ብርቱ ነው። ለጥበቡም ወሰን የለውም። ደግሞም ፍጻሜ በሌለው ሽልማት እና ደስታ የተሞላ ነው።
ሰው ሊያደርግ የሚችለውን ነገር በመፍራት ከእግዚአብሔር ፊትን ማዞር፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት የገባላቸውን የተስፋ ቃል ሁሉ ማቃለል ነው። ትልቅ ስድብ ነው። እንዲህ ባለው ስድብ ደግሞ እግዚአብሔር ሊደሰት አይችልም።
በሌላ በኩል፣ አለማመናችን በእግዚአብሔር ፊት የሚያመጣውን ነቀፋ በመፍራት፣ የተስፋ ቃሎቹን ስንሰማ እና በድፍረት ስንታመንባቸው፣ ያኔ እግዚአብሔር እጅግ ይከበራል። የላቀ ደስታንም ያገኛል።