በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን! (ዕብራውያን 9፥14)
ያለነው ስልጣኔ ባየለበት ዘመን ውስጥ ነው። ዘመኑ በኢንተርኔት እና በስማርት ስልኮች፣ በጠፈር ጉዞ እና በልብ ንቅለ ተከላ የተሞላ ዘመን ነው። ነገር ግን ቀንበራችን ከጥንት እንደነበረ አለ። ሕሊናችን ይወቅሰናል፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለን እንዲሰማን ያደርጋል። ከእግዚአብሔር ርቀናል፤ ኅሊናችን ደግሞ ይመሰክርብናል።
ራሳችንን ሺህ ጊዜ ብንቧጥጥ፣ ልጆቻችንን ለጣዖታት ወደ ወንዝ ብንገብር፣ ያለንን ሁሉ ለበጎ አድራጎት ሥራ ብንሰጥ፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችን በየዕለቱ ብንመግብ፣ ከአስደሳች ነገር ሁሉ ርቀን ራሳችንን ብንጎዳ እንኳ፤ ውጤቱ ያው ነው። ዕድፋችን አይለቅም፤ ሞትም ያስፈራራናል።
ሕሊናችን እንደረከሰ እናውቀዋለን። ርኩሰቱ ደግሞ ውጫዊ አይደለም። አስክሬን፣ ያደፉ ነገሮች፣ እሪያ ከመንካት ጋር በተያያዘ አይደለም። ኢየሱስ፦ ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው ብሏል (ማርቆስ 7፥15-23)። ሁለንተናችን በትምክህት፣ ስንፍና፣ ምሬት፣ ፍትወት፣ ምቀኝነት፣ ቅናት፣ መመኘት፣ ግድየለሽነትና ፍርሃት ረክሷል።
በዚህም የስልጣኔ ዘመን ሆነ ባለፉት ዓመታት፣ ብቸኛው መፍትሔ የክርስቶስ ደም ነው። የገዛ ህሊናችሁ ሲወቅሳችሁ ወዴት ትዞራላችሁ? ዕብራውያን 9፥14 መልሱን ይሰጣችኋል፦“በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!”
አሁንም ቢሆን ለዘለዓለም መልሱ፣ ወደ ክርስቶስ ደም መዞር ነው። በሕይወት ውስጥ እፎይታ፣ በሞት ውስጥ ደግሞ ሰላም ሊሰጣችሁ ወደሚችል፣ በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ውስጥ ወዳለው ብቸኛው የሕሊና አፅጂ ዘወር በሉ። እርሱን ብቻ ተመልከቱ፤ በእርሱ ታመኑ።