ብቸኛው ዘላቂ ደስታ | መስከረም 9

ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። (ዮሐንስ 16፥22)

“ደስታችሁን የሚወስድባችሁ የለም” ምክንያቱም የደስታችሁ ምንጭ ከኢየሱስ ጋር መሆናችሁ ነው። ኢየሱስ ከሞት ስለተነሣ እናንተም ፈጽሞ አትሞቱም፤ ከእርሱ ማንም፣ መቼም አይነጥላችሁም።

ስለዚህ ደስታችሁ ፈጽሞ ከእናንተ የማይወሰድ ከሆነ፣ ሁለት ነገሮች እውነት መሆናቸው የግድ ነው። አንደኛው፣ የደስታችሁ ምንጭ ዘላለማዊ መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እናንተም ዘላለማዊ መሆናችሁ ነው። እናንተ ወይም የደስታችሁ ምንጭ ጠፊ ከሆነ፣ ደስታችሁም እንዲሁ ጠፊ ይሆናል።

ነገ እንሞታለንና እንብላ፤ እንጠጣ፤ እንደሰት ብሎ ምን ያህሉ ሰው እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ይሆን? (ሉቃስ 12፥19)። መብል ለዘላለም አይቆይም፤ እኔም አላፊ ነኝ። ስለዚህ ያለንን አጭር ጊዜ በድሎት እናሳልፍ። እንዴት ያለ አሳዛኝ አስተሳሰብ ነው!

እንደዚህ ለማሰብ ከተፈተናችሁ፣ ይህንን ቆም ብላችሁ አስቡ፦ የደስታችሁ ምንጭ ከኢየሱስ ጋር መሆናችሁ እስከሆነ ድረስ፣ በዚህም ሆነ በሚመጣው ሕይወት “ደስታችሁን የሚወስድባችሁ የለም።”

ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ደስታ ሊነጥቀን አይችልም (ሮሜ 8፥38–39)።

ከኢየሱስ ጋር በመሆን ያለው ደስታ፣ ከአሁን እስከ ዘላለም የማይቋረጥ ጅረት ነው። በምንም ነገር አይቋረጥም። በሞትም ጭምር። በእርሱም ሞት አልተገታም፤ በእኛም ሞት አይቋረጥም።