የትዕግሥት ክፍያ | ግንቦት 29

እናንተ እኔን ለመጕዳት ዐስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው። (ዘፍጥረት 50፥20)

በዘፍጥረት 37-50 ላይ የሚገኘው የዮሴፍ ታሪክ፣ በእግዚአብሔር ሉአላዊነትና ወደፊት በሚገለጠው ጸጋው ላይ እምነት ሊኖረን የሚገባበትን ምክንያት ያስተምረናል።

ዮሴፍ ለባርነት የተሸጠው በወንድሞቹ ነበር። ይህም ትዕግስቱን ምን ያህል ሊፈታተነው እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ከጊዜ በኋላ ግን በጲጢፋራ ቤት ማንም የማያገኘው ምርጥ ሥራ ተሰጠው። ከዚያም በገጠመው ያልተጠበቀ ፈተና ወቅት በጽድቅ በመመላለሱ፣ በጲጢፋራ ሚስት ውሸት ወደ እሥር ቤት ተወረወረ። ይህም ትዕግስቱን የሚፈትነው ሌላ ከባድ መከራ ነበር።

አሁንም ግን ነገሩ ተገልብጦ ለመልካም ሆነለት። የእስር ቤቱ ኃላፊ ብዙ ኃላፊነትና ሥልጣንን ሰጠው። ቆይቶ ለፈርዖን ጠጅ አሳላፊ ህልምን ከፈታለት በኋላ፣ ለውለታው ምላሽ አገኛለሁ ብሎ ሲጠብቅ፣ ጠጅ አሳላፊው ግን ለሁለት ዓመታት ያህል ረሳው። ይህም ትዕግስትን የሚጠይቅ ሌላ ከባድ ፈተና ነበር።

በመጨረሻ ግን፣ የእነዚህ ሁሉ ፈተናዎችና የዘገዩ መልሶች ትርጉም ግልጽ ሆነለት። ዮሴፍ ከፈርዖን ቀጥሎ የግብፅ መሪ ለመሆን እየተሰራ ነበር። ለባርነት የሸጡትን ወንድሞቹንም ከረሀብ አዳናቸው። ለረጅም ጊዜ ያላያቸውን ወንድሞቹንም ሲያገኛቸው፣ እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ። … እናንተ እኔን ለመጕዳት ዐስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው” (ዘፍጥረት 45፥750፥20)።

ዮሴፍ እነዚህን ሁሉ የስደትና የመከራ ዓመታት እንዲታገስ ያደረገው ቁልፍ ነገር ምንድን ነው? መልሱ፦ በእግዚአብሔር ሉአላዊነትና ወደፊት በሚገለጠው ጸጋው ላይ ያለው እምነት ነው የሚል ነው። ባልታቀደ ጊዜና ቦታ የሚፈጠረውን አስቸጋሪ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ሚያስደንቅ ደስታ መለወጥ እንደሚችል አምኖ ነበር።

ለእኛም የትዕግስታችን ቁልፍ ይህ ነው። እጅግ አስጨናቂ እና ሕመም በበዛባቸው የመከራ ወቅቶቻችን ሁሉ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ስለኛ እየሠራ መሆኑን በእርግጥ እናምን ይሆን?