ፍጹም የሆነችው ከተማ | የካቲት 14

ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። (ዕብራውያን 11፥16)

አንዳች ብክለት የሌለባት፣ ቆሻሻ የማያውቃት፣ የተፋፋቀ የግድግዳ ቀለም ወይም ውድቅድቅ ያሉ የጭቃ ቤቶች የማይታዩባት፣ ስድድብና ድብድብ የማይሰማበት፣ ጾታዊ ጥቃት የማይፈጸምበት፣ እሳት አደጋ፣ ስርቆት፣ ግድያ፣ ውንብድና እና ወንጀል ፈጽሞ የማይኖርባት ከተማ ናት።

እግዚአብሔር ራሱ ስለሚኖርባት የእግዚአብሔር ከተማ ፍጹም ናት። እርሱ ይረማማድበታል፤ ይናገርባታል፣ በእያንዳንዱ ጎዳናዋ ራሱን ይገልጣል። እግዚአብሔር በውስጧ ይኖራልና፣ ሰላም፣ እውነትና ፍጹም ደስታ ይሞላታል። መልካም፣ ውብ እና ቅዱስ የሆነ ነገር ሁሉ መገኛ ነች።

ፍጹም ፍትህ በዚያ ስለሚኖር፣ በዚህ ዓለም ሕይወት፣ ለክርስቶስ በመታዘዝ የተከፈለ እያንዳንዱ መከራ በሺህ እጥፍ ይካሳል። ዋጋውም መቼም አይወርድም። እንደውም፣ በዘላለም ውስጥ በማያልቅ ደስታ የበለጠ እየፈካ እና እየደመቀ ይሄዳል።

በዚህ ምድር ላይ ካለ ከየትኛውም ነገር አስበልጣችሁ ይህችን ከተማ ስትፈልጉ፣ በዕብራውያን 11፥10 ላይ እንደተጻፈው፣ ይህችን ከተማ ያቀዳትን እና ያበጃትን እግዚአብሔርን ታከብራላችሁ። እግዚአብሔር ሲከብር ደግሞ ደስ ይለዋል፣ አምላካችሁም ተብሎ ሊጠራባችሁ አያፍርም።