የቃሉ የመውጋት ኃይል | ሕዳር 11

የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል። (ዕብራውያን 4፥12)

የእግዚአብሔር ቃል ብቸኛ ተስፋችን ነው። መልካም ዜና የሆኑት የእግዚአብሔር ተስፋዎች እናም ደግሞ የፍርድ ማስጠንቀቂያዎቹ ወደ ልቤ ዘልቀው ለመግባትና የኅጢአትን አታላይነት ግልጥልጥ አድርገው ለማሳያት የሚችሉ ሕያውና ስለታም መሳሪያዎች ናቸው።

ነገዬ ብሩኅ የሚሆነው በኀጢአት አይደለም። ውርጃ ነገን ብሩኅ አያደርግልኝም። ማጭበርበር፣ ተገላልጦ መሄድ፣ ዝሙትና መዳራት፣ ፍቺ፣ በቀለኝነትም ሆነ በመስሪያ ቤቴ ያለ ጉቦኝነትን አይቶ ዝም ማለት ነገን ብሩኅ አያደርግልኝም። ከዚህ መጭበርበር የሚታደገኝ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው።

በጭለማ ሲርመሰመሱ የነበሩ በረሮዎች ላይ ብሩኅ የፀሐይ ብርሃን በድንገት ቢገባ መግቢያ እንደሚጠፋቸው ሁሉ፣ የእግዚአብሔርም ቃል በልባችን ውስጥ እርካታን የሚሰጡ በማስመሰል የሚርመሰመሱ የኃጢአት በረሮዎችን መደበቂያ ያሳጣቸዋል። ልባችሁን ሊያደነድኑ እና ከእግዚአብሔር አርቀዋችሁ ወደ ጥፋት ሊወስዷችሁ ከሚሞክሩ ጥልቅ የኃጢአት ማታለያዎች ይጠብቋችሁ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ወንጌሉን፣ ተስፋዎቹንና ቃሉን ሰጥቷችኋል።

በእምነት ጎዳና ላይ መታገላችሁን በትጋት ቀጥሉ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ፣ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ስለሆነ፣ የትኛውም የኃጢአት ሽንገላ ከሄደበት ርቀት ይልቅ፣ በጥልቀት ዘልቆ በመግባት እውነተኛ ዋጋ ያለውን ደግሞም ሊታመን እና ሊወደድ የሚገባውን እውነት ይገልጣል።