“ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍጥረት 1፥27)።
እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ የፈጠረው፣ ዓለም እግዚአብሔርን በሚያጸባርቁ አካላት እንድትሞላ ነው። ማንም የፍጥረትን ግብ እንዳይስት፣ ስምንት ቢሊዮን የእግዚአብሔር አምሳሎች በዚህ ምድር ላይ አሉ።
ማንም ሰው ፈጽሞ ካልታወረ በስተቀር፣ የሰው ሁሉ ግብ እግዚአብሔርን ማወቅ፣ መውደድ እና ማሳየት መሆኑን ሊያጣው አይችልም። በኢሳይያስ 6፥3 መላዕክቱ፣ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለች” ሲሉ እንመለከታለን። ምድር በቢሊዮን በሚቆጠሩ የእግዚአብሔርን ምስል በተሸከሙ ሰዎች የተሞላች ነች።
ነገር ግን ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ተፈጥሮም ጭምር የእግዚአብሔርን ማንነት ያንጸባርቃል። ለምን እንዲህ ውብ የሆነ የመኖሪያ ዓለም አስፈለገ? ለምንስ አጽናፈ ዓለሙ እንዲህ ሰፊ ሆኖ ተሰራ?
እስከዛሬ ድረስ በምድር የኖሩት ሰዎች ሁሉ ከተናገሯቸው ቃላት እና ካወጧቸው ድምጾች ብዛት የሚበልጥ የከዋክብት ቁጥር እንዳለ አንድ ቦታ አንብቤአለሁ። ለምንድነው እንዲህ የበዙት? ለምንስ እንዲህ ገዘፉ? ሊታሰብ በማይችል ርቀት ላይ ሆነው ብርሃናቸው እንዲህ መግነኑስ ለምን አስፈለገ? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ በጣም ግልጽ ነው፦ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ” (መዝሙር 19፥1)።
“ለሕይወት ምቹ የሆነቸው ብቸኛዋ ፕላኔት ምድር ከሆነች እና ሰው ከከዋክብት መካከል ብቸኛው ፍጡር ከሆነ፣ ለምን እንደዚህ ያለ ትልቅ እና ባዶ አጽናፈ ዓለም አስፈለገ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ፣ የፍጥረት ሁሉ ዓላማ ስለእኛ ሳይሆን ስለእግዚአብሔር ነው የሚል ነው። ይህ ፍጥረት እንደውም በተገቢው መልኩ አይገልጠውም። እርሱ እጅግ የከበረ ነው። በኀይሉ ታላቅ ነው። ከመታወቅ በላይ ነው። የፊቱ ብርሃን ጋላክሲዎች ሁሉ ተደምረው ከሚለቁት የብርሃን ነጸብራቅ ይበልጣል። አንድ ብልህ ሰው እንዳለው፤ “እግዚአብሔር አጽናፈ ዓለሙን ልክ እንደ ለውዝ ፍሬ በኪሱ ይዟት ሊዞር ይችላል።”
እግዚአብሔር የፈጠረን እንድናውቀው እና እንድንወደው፣ እንዲሁም እርሱን እንድናሳይ ነው። ከዚያም ደግሞ፣ እርሱ ምን እንደሚመስል ፍንጭ ሊሰጠን አጽናፈ ዓለሙን ሁሉ ፈጠረ።