ታላቁ የተስፋ ጉልበት | መስከረም 21

ሥርዐትህን እሻለሁና በነፃነት እሄዳለሁ። (መዝሙር 119፥45 – የጸሐፊው ትርጉም)

የደስታ ዋና ክፍል ነፃነት ነው። ማናችንም ከምንጠላው ነገር ነፃ ካልወጣን፣ ለምንወደውም ነገር ነፃ ካልሆንን ደስተኛ አንሆንም።

እውነተኛ ነፃነትን የምናገኘው ከየት ነው? መዝሙር 119፥45 “ሥርዐትህን እሻለሁና በነፃነት እሄዳለሁ” ይላል።

ምስሉ ክፍት የሆነ ቦታ ይሰጣል። ቃሉ ከአእምሮ ጠባብነት ነፃ ያወጣናል። “አምላክ ለሰሎሞን… በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው” (1ኛ ነገሥት 4፥29)። ቃሉ ከሚያስፈሩ እስራቶች ነፃ ያወጣናል። “ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ” (መዝሙር 18፥19)።

ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ይላል (ዮሐንስ 8፥32)። እያሰበ ያለው ነፃነት ከኅጢአት ባርነት ነፃ መሆንን ነው (ዮሐንስ 8፥34)። ወይም በሌላ አነጋገር ለቅድስና የሚሆን ነፃነት ነው።

የእግዚአብሔር የጸጋ ተስፋዎች፣ ቅድስናን በተመለከተ ከፍርሀት እና ከባርነት ይልቅ የነፃነት ኃይል ይሰጣሉ። ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ተስፋዎች ውስጥ ያለውን የነፃነት ኃይል እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ካለው ምግባረ ብልሹ ሕይወት አምልጣችሁ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ በእነዚህ ነገሮች አማካይነት እጅግ ታላቅና ክቡር የሆነውን ተስፋ ሰጥቶናል” (2ኛ ጴጥሮስ 1፥4)።

በሌላ አነጋገር፣ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ስንደገፍ፣ የክፋት እና የኃጢአት ምኞትን በታላቁ የተስፋ ጉልበት እንደመስሳለን።

የዚህችን ዓለም የደስታዋን ጉልበት የሚሰብረው ቃል ምንኛ ወሳኝ ነው! መንገዳችንን ለማብራት እና ልባችንን በእግዚአብሔር ቃል ለመሙላት ምንኛ ንቁ መሆን አለብን!? “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝሙር 119፥105)። “አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” (መዝሙር 119፥11)።