ክርስቶስን ለመመስከር የሚያስችል ኅይል | ሐምሌ 16

ሐዋርያትም ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኀይል መመስከራቸውን ቀጠሉ፤ በሁላቸውም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበር።” (ሐዋርያት ሥራ 4፥33)

ምናልባት ነገ የሚኖረን አገልግሎት መልካም ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለ ክርስቶስ መመሥከር ከሆነ፣ ቁልፉ ነገር የእኛ ማስተዋልና ክህሎት ሳይሆን ለዛ ቀን የተመደበልን የተትረፈረፈ ጸጋ ነው።

ከሞት ስለ ተነሣው ክርስቶስ አሳማኝ ምስክርነት ለመስጠት ሐዋርያት ምንም ዓይነት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አይመስልም ነበር። ለሦስት ዓመታት አብረውት ቆይተዋል፤ ሲሞት አይተውት ነበር፤ ከሞቱም በኋላ የትንሳኤው ምሥክሮች ነበሩ። በምስክርነት ቋታቸው ውስጥ “ብዙ ማስረጃዎች” ነበሯቸው (ሐዋሪያት ሥራ 1፥3)። በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ያዩት ክብር የምስክርነታቸውን ቃል ለማጽናት በራሱ በቂ ይሆናል ብላችሁ እስክታስቡ ድረስ ኀይለኛ ልምምድ ነበራቸው።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚነግረን ግን ይህን አይደለም። በታማኝነት እና በውጤታማነት የመመስከር ኃይል በዋነኝነት የመጣው ከጸጋ ትዝታዎች አልነበረም። የትላንቱ ጸጋ አልነበረም ታላቅን ነገር ያደረገው። ይልቁንም ዕለት በዕለት ከሚሰጠው እና ሁልጊዜ አዲስ ከሆነው ከ“ታላቅ ጸጋ” የተነሣ ነው። “በሁላቸውም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበር” ይናል። ለሐዋርያት የሆነው እንዲህ ነበር። ለእኛም በምስክርነት አገልግሎታችን የሚሆነው እንዲሁ ነው።

ስለክርስቶስ የምንመሰክረውን ምስክርነት ለማጽናት እግዚአብሔር ተጨማሪ ምልክቶች እና ድንቆችን ቢያመጣ፣ ወደኛ የሚመጡት ልክ ለእስጢፋኖስ በመጡበት መንገድ ነው። “በዚህ ጊዜ እስጢፋኖስ ጸጋንና ኀይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን ያደርግ ነበር” (ሐዋርያት ሥራ 6፥8)።  እስጢፋኖስ ለሚያስፈልገው ነገር ሁሉ፣ በስተመጨረሻም ለመሞት የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመሙላት፣ ጸጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተሰጥቶት ነበር።

ልዩ በሆነ የአገልግሎት ተግዳሮት ወቅት የምንደገፍበት ልዩ የሆነ ጸጋና ኃይል አለ። ይህም እግዚአብሔር “የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግጥላቸው” የነበረበት አዲስ የኃይል ተግባር ነው (ሐዋርያት ሥራ 14፥3ዕብራውያን 2፥4)። ሁልጊዜም የሚገለጠው የኃይሉ ጸጋ ሁልጊዜም ለሚሰጠው የእውነት ጸጋ ማረጋገጫ ነው።