ወንድሞቻችንን ስለምንወድድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። (1ኛ ዮሐንስ 3፥14)
ስለዚህ፣ ፍቅር ዳግም የመወለዳችን፣ ክርስቲያን የመሆናችን እና የመዳናችን ማስረጃ ነው ማለት ነው።
አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅድስናችንን እና ለሰዎች ያለንን ፍቅር እስከ መጨረሻ ለመዳናችን እንደ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ያስቀምጠዋል። በሌላ አነጋገር፣ ቅድስና እና ፍቅር ከሌለን፣ በፍርድ ቀን መዳን አንችልም ማለት ነው (ለምሳሌ፦ ዕብራውያን 12፥14፤ ገላትያ 5፥21፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፥10)። ታዲያ ይህ ማለት ግን፣ ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቀው በኑሯችን ወይም በፍቅራችን ነው ማለት አይደለም። በፍጹም እንዲህ ሊሆን አይችልም። ሰው በመቀደስ ወይም በመልካም ሥራ ሊድን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኤፌሶን 2፥8-9 ባሉ ክፍሎች በግልጽ ደጋግሞ እንደሚናገረው፦ “በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም።” በፍጹም በሥራ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የዳንነው በእምነት እንደሆነና እስከ መጨረሻ ለመዳን ሰዎችን መውደድ እንዳለብን ሲናገር፣ በእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት እርግጥ ከመሆኑ የተነሳ የሚያመነጨው ፍቅር የእምነታችንን እውነተኛነት ያረጋግጣል ማለቱ ነው።
ስለዚህ፣ በሚያስፈልገን ጊዜ የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ለማገኘት ሌሎችን ልንወድድ ይገባናል፤ ይህም የሚሆነው ቀዳሚው ቅድመ ሁኔታ የሆነው እምነት እውነተኛ መሆኑን ስለሚያረጋግጥ ነው። ለሌሎች ያለንን ፍቅር እንደ ሁለተኛ ቅድመ ሁኔታ ልንቆጥረው እንችላለን። የመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታ የሆነውንና ብቻውን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሚያደርገን እምነት በእርግጥ መኖሩን ያረጋግጥልናል።
እምነት በእግዚአብሔር የጸጋ ተስፋዎች ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ክብር ይመለከታል። ደግሞም፣ በእነዚህ ተስፋዎች የተገለጠውን የእግዚአብሔርን የማዳን ስራ ያረጋግጥልናል። የእግዚአብሔርን ክብር በመንፈሳዊ ዓይኖቻችን ማየትና በዚያም መደሰት፣ የጸጋው ተቀባዮች ለመሆን እንደተጠራን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ይህ ማስረጃ እግዚአብሔር በገባው ቃል ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንደገፍ ነፃ ያደርገናል። በተስፋው ላይ መደገፋችን ደግሞ ሌሎችን እንድንወድ አቅም ይሰጠናል። ይህም መልሶ እምነታችን እውነተኛ መሆኑንን ያረጋግጣል።
እነዚህን ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ የሚይዝን እምነት ዓለም በብዙ ጭንቀት ትፈልጋለች፦ ይህንን አስገራሚ የማይናወጥ መለኮታዊ እውነት የሚያዩ ዓይኖችን እና ተግባራዊ የሕይወት ለውጥ የሚያመጣ ኅይል ትሻለች። እኛም የምንፈልገው ይህንኑ ነው። ለዛም ነው ክርስትያን የሆንነው።
በእርሱ ለሚታመኑ ረዳት አልባ ሰዎች የገባውን ቃል በመፈጸም የራሱን ድንቅ ውበት እና ዘላለማዊ በቂነት የሚያጎላ ኃያል የጸጋ አምላክ አለ። ስሙም እግዚአብሔር ነው። የማይነካው፣ የማይለውጠው፣ የማያድሰው የህይወት ክፍል የሌለው አምላክ ነው። ይህንንም አምላክ በማክበር የሚገኝ ኃይል አለ። ይህ አስደናቂ አምላክ ተግባራዊ በሆኑ መንገዶች ሰዎችን ሁሉ መውደድ የምንችልበትን ኃይል ይሰጠናል።