የሀብት ዋና ግብ | ጥቅምት 11

ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም።” (ኤፌሶን 4፥28)

ከሀብት ጋር ለመኖር ሦስት መንገዶች አሉ፦

  1. ሰርቆ ማከማችት ትችላላችሁ
  2. ሠርታችሁ ልታገኙ ትችላላችሁ ወይም ደግሞ
  3. ለመስጠት ስትሉ ሠርታችሁ ማግኘት ትችላላችሁ።

አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ሁለተኛው መንገድ ላይ ይገኛሉ። ከመስረቅ ይልቅ ሥራን እናበረታታለን፤ በታማኝነት ሠርተን ከተከፈለን በክብር የተመላለስን ይመስለናል። ሐዋሪያው ግን የሚነግረን ይህንን እንድናደርግ አይደለም።

ባህላችን ሁሉ በሁለተኛው መንገድ እንድንረማመድ ያስገድደናል፦ ሠርቶ ማግኘት። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ወደ ሦስተኛው መንገድ ይገፋፋናል፦ ሠርቶ አግኝቶ ወደ መስጠት። “ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” (2ኛ ቆሮንቶስ 9፥8)።

እግዚአብሔር በተትረፈረፈ ሙላት የሚባርከን ለምንድን ነው? ለመኖር በቂ እንዲኖረን እና የቀረውን የሌሎችን ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሥቃይ እንድንቀንስበት፣ ብሎም መልካም ሥራ እንድንሠራበት ነው። ለእኛ የሚበቃንን አግኝተን፤ ለሌሎች እንድንደርስ የተትረፈረፈ ነው።

ችግሩ አንድ ሰው የሚያገኘው ገቢ አይደለም። ትልልቅ ሥራዎች እና ትልልቅ ገቢዎች በዚህ ዘመን የተለመዱ ናቸው፤ በራሳቸው ክፉ ነገሮች አይደሉም። ክፉ የሚሆነው በትልቅ ደምወዝ የቅንጦት ሕይወት መኖር እንዳለብን ሲሰማን ነው።

እግዚአብሔር የፀጋው መተላለፊያ ገመዶች አድርጎናል። አደጋው ይህ መተላለፊያ በወርቅ የተለበጠ መሆን አለበት ብለን ስናምን ነው። የግድ በወርቅ መሆን የለበትም፤ በመዳብም ቢሆን ይበቃል። መዳብ በጣም ጥሩ አስተላላፊ ነው። እናም በመስጠታችን ውስጥ ታላቁን በረከት እንቀበላለን (ሐዋርያት 20፥35)።