የመጨነቅ ዋና ችግር | ጥቅምት 27

እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? (ማቴዎስ 6፥30)

የጭንቀት ሁሉ ሥር መሠረቱ አባታችን እግዚአብሔር ወደፊት ሊሰጠን ያለውን ጸጋ አለማመን ወይም የእምነት ማነስ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል።

ለዚህ እውነት አንዱ ምላሻችን ሊሆን የሚችለው፦ “ይህማ መልካም ዜና አይደለም! እንዲያውም በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ዜና ነው። እየታገልኩ ያለሁት ከጭንቀት ጋር ብቻ ነው ብዬ ነበር ማስበው እንጂ፣ ችግሩ ከዚያ የጠለቀ በእግዚአብሔር ላይ ያለኝን መታመን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ በጣም ልብ ይሰብራል” የሚል ሊሆን ይችላል።  

ከዚህ ተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር እስማማለሁም፣ አልስማማምም።

እስቲ ሆዳችሁን በተደጋጋሚ ለረጅም ጊዜ አመማችሁ እንበል። አንዳች ላይፈይድላችሁ ሁሉንም ዐይነት መድኃኒት ሞከራችሁ፣ ምግብ ስትመርጡም ከረማችሁ። ከዚያ አንድ ሐኪም በትንሿ አንጀታችሁ ውስጥ ካንሰር እንዳለባችሁ ነገራችሁ። ይህን እንደ መልካም ዜና ትቆጥሩታላችሁ? በፍጹም አትቆጥሩትም። እኔም መልካም ዜና አለመሆኑ ላይ እስማማለሁ።

ነገር ግን ይህንኑ ጥያቄ በሌላ መንገድ ልጠይቅ። ሐኪሙ ገና ሊታከም በሚችልበት ጊዜ ካንሰሩን በማግኘቱ እና በእርግጥ በተሳካ ሁኔታ ሊታከም የሚችል በመሆኑ ደስተኛ ናችሁ? አዎ፣ ዶክተሩ ትክክለኛውን ችግር በማግኘቱ በጣም ደስተኛ ነኝ ትላለችሁ። አሁንም እስማማለሁ።

ስለዚህ ካንሰር እንዳለባችሁ የሚነግራችሁ ዜና መልካም ዜና አይደለም። ነገር ግን፣ በሌላ መልኩ፣ መልካም ዜና ነው፤ ምክንያቱም የችግሩን ትክክለኛ ቦታ እና መንስኤ ማወቁ ጥሩ ነው፤ በተለይም ደግሞ ችግሩ በተሳካ ሁኔታ ሊታከም የሚችል ችግር ሲሆን ማለት ነው።

ከጭንቀት በስተጀርባ ያለው እውነተኛ ችግር በእግዚአብሔር የወደፊት የጸጋ ተስፋዎች ላይ ያለ “ትንሽ እምነት” መሆኑን መማር ከዚህ ምሳሌ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህንም የነገረን ራሱ ኢየሱስ ነው። ይህን ተረድተን፣ ወደ እርሱ “አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው!” ብለን ስንጮህ፥ ታላቁ እግዚአብሔር በሚያስደንቅ የፈውስ መንገዶች በልባችን ውስጥ መስራት ይችላል (ማርቆስ 9፥24)።