የትዕቢት መፍትሔ | ጥር 18

እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ። ይልቁንም፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። (ያዕቆብ 4፥13-16)

ያዕቆብ፣ ስለ ትዕቢትና ኩራት እንዲሁም እንዴት ድብቅ በሆኑ መንገዶች እንደሚታዩ እየተናገረ ነው። “በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።”

ራስን ለመታመን የምንፈተንባቸውን ሶስት ክፍሎች – ጥበብ፣ ኃይል እና ሀብትን – ብንወስድ፣ የመጨረሻ የትምክህት ጥግ የሆነውን አምላክ የለሽነትን በኅይል ይቀሰቅሳሉ። በራሳችን ዓይን የበላይ ሆነን ለመቀጠል ያለው ብቸኛ መንገድ የበላያችን የሆነን ማንኛውም ነገር መካድ ነው።

ለዚህም ነው ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎች ጊዜያቸውን ሌሎችን የበታች አድርጎ በመመልከት የሚያሳልፉት። ሲ. ኤስ. ሌዊስ እንዳለው፣ “ኩሩ ሰው ሁል ጊዜ ነገሮችን እና ሰዎችን ወደ ታች ይመለከታል፣ ወደ ታች እያየን ከሆነ ደግሞ ከላያችን ያለን መመልከት አንችልም።” (ክርስትና ለጠያቂ አእምሮ) ትዕቢት ባለበት እንዲጸና ከተፈለገ፣ በቀላሉ ከላይ ምንም የሚታይ ነገር እንደሌለ ማወጅ ብቻ በቂ ይመስለኛል። “ክፉ ሰው ከትዕቢቱ የተነሣ እግዚአብሔርን አይፈልግም፤ በሐሳቡም ሁሉ አምላክ የለም” (መዝሙር 10፥4)። በስተመጨረሻ፣ ትዕቢተኞች አምላክ እንደሌለ ራሳቸውን ማሳመን አለባቸው።

ለዚህም አንዱ ምክንያት እግዚአብሔር የመኖሩ እውነታ በሁሉም የህይወት ክፍሎቻቸው ውስጥ ጣልቃ የሚገባ በመሆኑ ነው። ትዕቢት ጥቃቅን ተራ የህይወት ጉዳዮችን ይቅርና፣ ፍጥረተ ዓለምን በመምራት ያለውን የእግዚአብሔርን የቅርብ ተሳትፎ ሊታገሥ አይችልም።

ትዕቢት የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት አይወድም። ስለዚህ፣ ትዕቢት የእግዚአብሔርን መኖር አይወድም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው። ይህንን ደግሞ “እግዚአብሔር የለም” በማለት ሊገልጸው ይችላል፤ አልያም “ለገና ወደ አትላንታ እየነዳሁ እሄዳለው” በማለት ይገልጸዋል።

ያዕቆብ “እርግጠኛ አትሁኑ” ይላል። ይልቁንስ፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ለገናም ወደ አትላንታ እንሄዳለን” ማለት አለብን።

የያዕቆብ ዋና ሃሳብ፣ ወደ አትላንታ መድረስ መቻላችሁን እና ይህንን ንባብ እንኳ አንባባችሁ እስክትጨርሱ በሕይወት መቆየታችሁን የሚወስነው እግዚአብሔር ነው የሚል ነው። ይህ የትዕቢትን በራስ መታመን እጅግ ያደቃል – ይህንን አንብባችሁ እስክትጨርሱ እንኳ ልባችሁ መምታቱን መቆጣጠር አትችሉም!

ያዕቆብ እግዚአብሔር የወደፊታችሁን ጥቃቅን ሁኔታዎች የማስተዳደር ሉዓላዊ መብቶች እንዳሉት አለማመን ትዕቢት ነው ይላል።

ይህንን ትዕቢት ለመዋጋት መንገዱ፣ በሁሉም የሕይወት ክፍሎች ውስጥ ለእግዚአብሔር ሉዓላዊነት መገዛትና በእኛ ምትክ እርሱ ኃይሉን እንደሚያሳይ (2ኛ ዜና 16፥9)፣ በየቀኑ ቸርነትና ምሕረቱ እንደሚከተሉን (መዝሙር 23፥6)፣ ለሚጠባበቁት እንደሚደርስላቸው (ኢሳይያስ 64፥4)፣ ለክብሩ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ እንደሚያስታጥቀን (ዕብራውያን 13፥21)፣ በገባው የማይነጥፍ የተስፋ ቃል ላይ ማረፍ ነው።

በሌላ አነጋገር፣ ለትዕቢት መድሐኒቱ፣ እግዚአብሔር ወደ ፊት በሚሰጠው ጸጋ ላይ ያለ የማይናወጥ እምነት ነው።