የምስጋና ቢስነት ሥር | ሕዳር 21

እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። (ሮሜ 1፥21)

ምስጋና ከሰው ልብ ውስጥ ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር ሲያርግ፣ እርሱ የበረከታችን ምንጭ ሆኖ ከፍ ከፍ ይላል። እርሱ ሠጪ እና ረጂ በመሆኑ ክቡርነቱ ይታወቃል።

ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኛ ላለው ታላቅ ቸርነት ምስጋና ከልባችን ውስጥ ካልወጣ፣ ምናልባት ለእርሱ ምስጋና ልንሰጠው፣ እርሱን እንደ ረጂ ልናገንነው አንፈልግም ማለት ነው።

የሰው ልጅም በባህሪው እግዚአብሔርን በምስጋና ከፍ ለማድረግ ወይም እርሱን እንደ ረጂ ሊያከብረው የማይፈልግበት ጥሩ ምክንያት አለ። ይህም ምክንያት ከራሳችን ክብር ስለሚቀንስብን ነው፤ ሰዎች ሁሉ ደግሞ በባህሪያቸው ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የራሳቸውን ክብር የሚወዱ ናቸው።

ከሁሉም ምስጋና ቢስነት ሥር፣ የራስን ታላቅነት መውደድ አለ። እውነተኛ አመስጋኝነት በባሕርይው የማይገባን ውርስ ወራሾች መሆናችንን ያምናል። እኛ የመስቀል ቅርጽ ባለው በኢየሱስ ክርስቶስ ምርኩዝ ላይ የተደገፍን አካል ጉዳተኞች ነን። በየደቂቃው በእግዚአብሔር ምሕረት የመተንፈሻ መሳሪያ ውስጥ የምንኖር ሽባዎች ነን። ጨቅላ ሕጻን በጋሪ ውስጥ እንደሚተኛ፣ በመንግሥተ ሰማይ ጋሪ ውስጥ የተኛን ልጆች ነን።

ተፈጥሯዊው ሰው፣ የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ ካላገዘው በቀር ራሱን እንደማይገባው ተጠቃሚ፣ አካል ጉዳተኛ፣ ሽባ ልጅ ማሰብ እጅግ ይጠላል። ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር በመስጠት ክብሩን ስለሚነጥቁት እነዚህን ምስሎች አይወዳቸውም።

ስለዚህ ሰው የራሱን ክብር ሲወድ፣ የራስ ብቁነቱን ሲያደንቅና ራሱን እንደ የኃጢአት በሽተኛና አቅመ ቢስ አድርጎ ማሰብን ሲጠላ፣ ለእውነተኛው አምላክ እውነተኛ ምስጋናን ለማቅረብ ፈጽሞ አያስብም፤ ራሱን ብቻ እንጂ እግዚአብሔርን እንደሚገባው መጠን ከፍ አያደርገውም።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” (ማርቆስ 2፥17) ።

ኢየሱስ የመጣው ደህና ነን ብለው ድርቅ የሚሉትን ለማገልገል አይደለም። ከእኛ የሚፈልገው አንድ ታላቅ ነገር፣ ታላቅ አለመሆናችንን አምነን እንድንቀበል ነው። ይህ ለትዕቢተኞች መርዶ ነው፤ ነገር ግን ራስ የመቻል ማስመሰላቸውን ትተው እግዚአብሔርን ለሚፈልጉ ከማር የጣፈጠ የምስራች ነው።