ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም። (ዮሐንስ 6፥35)
እምነት ማለት እግዚአብሔር በክርስቶስ ለእኛ በሆነው ነገር ሁሉ መርካት ማለት እንደሆነ ከዚህ ክፍል እንመለከታለን።
እምነትን በዚህ መንገድ መመልከት ሁለት ነገሮችን አጉልቶ ያሳያል። በመጀመሪያ፣ የእምነት ዋና መካከለኛ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ እንመለከታለን። የሚያረኩን የእግዚአብሔር ተስፋዎች ብቻ መሆናቸው ይቀርና፣ ራሱ እግዚአብሔር በኢየሱስ ለእኛ የሆነው ሁሉ የእርካታችን ምንጭ ይሆናል። እምነት፣ እግዚአብሔር ቃል የገባልንን ስጦታዎች ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ራሱን በክርስቶስ በኩል ሐብታችን ያደርገዋል።
እምነት ተስፋውን የሚጥለው በሚመጣው ዘመን ላይ በሚኖረን ርስት ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ራሱ የመኖሩ እውነታ ላይ ነው። “እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል” (ራዕይ 21፥3)።
አሁን እንኳን ቢሆን፣ እምነት አጥብቆ የሚይዘው ኃጢአቶቻችን ሁሉ ይቅር መባላቸውን ብቻ ሳይሆን (በራሱ ውድ መሆኑ እንዳለ ሆኖ)፣ ነገር ግን የዘላለማዊው ክርስቶስ በልባችን መገኘት እና የራሱ የእግዚአብሔር ሙላት ነው። በኤፌሶን 3፥17-19 ጳውሎስ “በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር . . . እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ” ብሎ የሚጸልየው ለዚህ ነው።
በእርግጥም እምነት ማለት እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ለእኛ በሆነው ነገር ሁሉ መርካት ማለት ነው። ይህ አረዳድ በሁለተኝነት፣ ስለ እርካታ ያልንንም አመለካከት ይቀይረዋል። እምነት ማለት የነፍሳችንን ጥማት በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ምንጭ ማርካት ማለት መሆኑን እንረዳለን። በዮሐንስ 6፥35 ላይ “ማመን” ማለት የሕይወትን እንጀራ ለመብላት እና የሕይወትን ውኃ ለመጠጣት ወደ ኢየሱስ መምጣት ማለት እንደሆነ እናያለን (ዮሐንስ 4፥10፣ 14)። እነዚህም ከኢየሱስ በቀር ሌላ ሊሆኑ አይችሉም።
ኀጢአትን ማራኪ የሚያስመስልብንን ባርነት የሚሰብረው የእምነት ኅይል ምስጢር ይህ ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ለእኛ በሆነው ነገር ሁሉ ልባችን ሲረካ፣ ከክርስቶስ ጥበብ ሊያርቀን የሚያባብለን የኃጢአት ቀንበር ሁሉ ይሰባበራል።