እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ። (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)
የክርስቲያኖችን መከራ በተመለከተ የእግዚአብሔር ሐሳብ ይህ ነው፦ በራሳችን እና በዓለም መደገፍ አቁመን በእርሱ እንድንመካ ይፈልጋል። አንድም ሰው፣ “ስለ ሕይወት ብዙ ጥልቅ ነገሮችን የተማርኩት በምቾትና በድሎት ውስጥ ሆኜ ነው” ሲል ሰምቼ አላውቅም።
በተቃራኒው ደግሞ፣ የበረቱ ቅዱሳን፣ “የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመረዳት እና በእርሱ እውቀት ለማደግ በመከራ ውስጥ ማለፍ ነበረብኝ” ሲሉ ግን ሰምቻለሁ።
ከሁሉ የተወደደው ዕንቁ የክርስቶስ ክብር ነው።
ጳውሎስ በመከራችን ሁሉን የሚያስችለውን የክርስቶስ ፀጋ ክብር እንደምናጎላ ይነግረናል። በችግራችን ጊዜ በእርሱ ላይ ከተደገፍን፣ በተስፋ እንድንደሰት ጽናቱን ይሰጠናል። በዚህም ጸጋን እና ኅይልን የሚቸር ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑ ይታያል።
ነፍሳችን በተጨነቀች ጊዜ በእርሱ መታመናችንን ከቀጠልን፤ በእውነትም እርሱ ካጣነው ነገር ሁሉ የሚበልጥ መሆኑን እናሳያለን።
ክርስቶስ በመከራ ውስጥ ለነበረው ሐዋርያ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለው። ጳውሎስ ለዚህ ሲመልስ እንዲህ አለ፦ “ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ። ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9-10)።
ስለዚህ መከራ በእግዚአብሔር የተዘጋጀው ክርስቲያኖችን በራሳቸው ከመመካት አንስቶ ወደ ፀጋ ለማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ፀጋ ልቆ እንዲታይ እና እንዲያበራ ነው። እምነት የሚያደርገው ይህንን ነው፤ የክርስቶስን ክብር ያጎላል።
በእግዚአብሔር ሕይወት ውስጥ ያሉት ጥልቅ ነገሮች የሚገለጡት እና የሚጎሉት በመከራ ውስጥ ነው።