ትንሹ እምነት | ጥር 3

እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው። (ሮሜ 9፥16)

እንደ ኢየሱስ አማኞች በዚህ ዓመት ከእግዚአብሔር የምናገኘው ነገር ሁሉ ምሕረት መሆኑን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ግልጽ እናድርግ። በመንገዳችን ላይ ምንም ዓይነት ደስታም ሆነ ሕመም ቢመጣ ሁሉም ምሕረት ናቸው።

ኢየሱስ ለዚህ ነው ወደ ዓለም የመጣው፦ “አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ” (ሮሜ 15፥9)። “ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ” ዳግም ተወልደናል (1ኛ ጴጥሮስ 1፥3)። “ምሕረትን እንድንቀበል” በየዕለቱ እንጸልያለን (ዕብራውያን 4፥16)፤ አሁንም ደግሞ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰንን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት እንጠባበቃለን” (ይሁዳ 1፥21)። ማንም ክርስቲያን ታማኝ ሆኖ ቢገኝ “ከጌታ ምሕረት የተነሣ ታማኝ” ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 7፥25)።

በሉቃስ 17፥5-6 ሐዋርያት ጌታን፣ “እምነታችንን ጨምርልን” ብለው ይማጸኑታል። ኢየሱስም፣ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ሾላ፣ ‘ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ተተከል’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” ይላቸዋል። በሌላ አነጋገር፣ የክርስትና ሕይወታችንና የአገልግሎታችን ችግር፣ የእምነታችን ጥንካሬና መጠን አይደለም፤ ምክንያቱም ዛፎችን የሚነቅለው ይህ አይደለም። እግዚአብሔር እንጂ። ስለዚህ፣ በእውነት ከክርስቶስ ጋር የምታገናኘዋ ትንሿ እምነት ለሚያስፈልጋችሁ ነገር ሁሉ ኃይሉን በበቂ ሁኔታ ትይዛለች። ጌታን በተሳካ ሁኔታ የታዘዝንባቸው ጊዜያትስ? ታዛዥነታችን ምሕረትን ከሚቀበሉት ወገን ያወጣናልን? ኢየሱስ በሉቃስ 17፥7-10 ይህን ይመልሳል።

“ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ዐራሽ ወይም በግ ጠባቂ የሆነ አገልጋይ ቢኖረው፣ ከዕርሻ የተመለሰውን አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ወደ ማእድ ቅረብ’ ይለዋልን? ከዚህ ይልቅ፣ ‘እራቴን እንድበላ አዘጋጅልኝ፣ እኔ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፤ ትጠጣለህ’ አይለውምን? እንግዲህ ይህ ሰው፣ አገልጋዩ የታዘዘውን በመፈጸሙ መልሶ ያመሰግነዋልን? ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቍጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ።’ ”

ስለዚህ፣ እንዲህ ብዬ ሐሳቤን ልጠቅልል፣ ሙሉ በሙሉ መታዘዝ እና ትንሿ እምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ዓይነት ነገርን ያስገኛሉ፦ ምሕረትን። አንድ የሰናፍጭ ዘር የምታህል እምነት የእግዚአብሔርን ዛፍ የሚያንቀሳቅስ ኃይል በምሕረት ታመጣለች። እንከን የለሽ ታዛዥነት ደግሞ በምሕረት ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ እንድንሆን ያደርገናል። ዋናው ነጥብ ይህ ነው፦ የእግዚአብሔር የምሕረቱ ጊዜም ሆነ ዓይነት ምንም ይሁን ምን ከምህረቱ ተጠቃሚዎች መሆናችንን አናቆምም። ሁልጊዜ በማይገባን ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ነን።

ስለዚህ ራሳችንን አዋርደን በደስታ፣ “እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ እናክብረው!”