እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው። (መዝሙር 27፥4)
እግዚአብሔር ለነፍስ ናፍቆት ምላሽ የማይሰጥ ንፉግ አይደለም። እርሱ መጥቶ የኃጢአትን ሸክም አንሥቶ፣ ልባችንን በደስታና በምስጋና ይሞላል። “ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤ ማቄን አውልቀህ ፍስሓን አለበስኸኝ፤ እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፤ ዝምም አትበል፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ” (መዝሙር 30፥11-12)።
ደስታችን ወደ ኋላ ዞር ብለን ከምናየው ውለታ ብቻ የሚመነጭ አይደለም። በተስፋ ወደ ፊት ከማየትም ይመነጫል፦ “ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤ አዳኜና አምላኬን፣ ገና አመሰግነዋለሁና” (መዝሙር 42፥5-6)።
“እግዚአብሔርን ደጅ እጠናለሁ፤ ነፍሴም በትዕግሥት ትጠብቀዋለች፤ በቃሉም ተስፋ አደርጋለሁ“ (መዝሙር 130፥5)።
በስተ መጨረሻ፣ ልብ የሚሻው የእግዚአብሔርን መልካም ስጦታዎች ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔርን ነው። እርሱን ማየት እና ማወቅ፣ ደግሞም በፊቱ መሆን የነፍስ ታላቁ ፌሽታ ነው። ከዚህ የበለጠ ተልዕኮ የለም። ቃላት አይገልጹትም። እርካታ፣ ሐሴት እና ደስታ በሚሉ ቃላት ልንገልጸው ብንሞክር እንኳ ከንግግር የሚያልፈውን እውነታ የመሸከም አቅሙ የላቸውም።
“እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው” (መዝሙር 27፥4)።
“የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ” (መዝሙር 16፥11)። “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ” (መዝሙር 37፥4)።