ስኬታማው የእግዚአብሔር ውድቀት | ታሕሳስ 20

ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

ፊልጵስዩስ 2፥9-11

የእግዚአብሔር ስኬታማ ውድቀት መጀመሩ የተበሰረው በገና ነው። ኀይሉን ማሳየት የሚወደው ሽንፈት በሚመስል መንገድ ነው። ስትራቴጂያዊ ድሎችን ለመጎናጸፍ ስልታዊ ማፈግፈግን ይተገብራል።

ከዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች መካከል አንዱ የሆው ዮሴፍ በሕልሙ ብዙ ክብር እና ሥልጣን ቃል ሲገባለት በብሉይ ኪዳን እናነባለን (ዘፍጥረት 37፥5-11)። ነገር ግን ያንን ድል ለመጎናጸፍ በግብፅ ባሪያ መሆን ነበረበት። ያ ብቻ ደግሞ በቂ አልነበረም፤ በሐቀኝነቱ ምክንያት የነበረበት አስከፊ ሁኔታ ትንሽ መሻሻል ሲያሳይ ከባርነትም ወርዶ እስረኛ ሆነ።

ነገር ግን ይህ ሁሉ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ፣ ከዚያም አልፎ ለዓለም ሁሉ የሚተርፍ መልካምን ነገር እንዲያመጣ በእግዚአብሔር የታቀደ ነበር። ምክንያቱም የፈርዖንን ጠጅ አሳላፊ ሊተዋወቅ የቻለው በእስር ሳለ ነበር። በኋላም ይህ ሰው ነው ዮሴፍን ወደ ፈርዖን የሚያቀርበው። ፈርዖንም በግብፅ ሁሉ ላይ ሾመው። በስተመጨረሻም ሕልሙ ተፈጸመ። ወንድሞቹ ሰገዱለት፤ እርሱም ከረሃብ ታደጋቸው። ዮሴፍ የክብርን ማማ የተቆናጠጠው ባልተለመደ መንገድ ነበር።

ይህ መንገድ ግን የእግዚአብሔር መንገድ ነው፤ ለልጁም ጭምር። ራሱን ባዶ አድርጎ የባርያን መልክ ያዘ። ከባርያም የባሰ እስረኛ ነበር። አልፎም በሞት ተቀጣ። እንደ ዮሴፍም ታማኝ ሕይወት ኖረ። “ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ” (ፊልጵስዩስ 2፥9-10)።

እግዚአብሔር ለእኛም ያስቀመጠው ይህንኑ መንገድ ነው። ክብር ቃል ተገብቶልናል፤ ነገር ግን ያ የሚሆነው በሮሜ 8፥17 በግልጽ እንደሚነግረን አብረነው መከራን ከተቀበልን ብቻ ነው። ወደ ላይ መንገዱ በሥር በኩል ነው። ወደ ፊት የምንሄደው በኋላ በኩል ነው። ስኬት ላይ የሚደረሰው መለኮታዊ ዕቅድ ውስጥ ባለው የውድቀት መንገድ ነው። እነዚህ መንገዶች ሁልጊዜ ሲታዩ የውድቀት መንገድ ይመስላሉ።

ነገር ግን በዚህ የገና በዓል ከዮሴፍ እና ኢየሱስ የምንማረው አንድ ነገር ካለ ይህ ነው። ሰይጣን እና ኀጢአተኛ ሰዎች ለክፋት ያቀዱትን እና ያሰቡትን፣ “እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው” (ዘፍጥረት 50፥20)።

እናንተ ፈሪ ቅዱሳን በርቱ
የምትፈሯቸው ደመናዎች ሁሉ
በምሕረት ተሞልተው በቅርቡ ይፈስሳሉ
ብዙ በረከትን ከላይ ያወርዳሉ።