የእግዚአብሔር ውብ የእጅ ሥራ | የካቲት 18

ነገር ግን ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ የለየኝ እና በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር። (ገላትያ 1፥15)

የጳውሎስን መለወጥ፣ የክርስቶስን ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም የጳውሎስ ኃጢአቶች ከእናንተ ድነት ጋር ምን እንደሚያገናኛቸው እስኪ በጥልቀት አሰላስሉ።

ጳውሎስ፣ እግዚአብሔር ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እንደለየው እና ከዚያም ደግሞ ከዓመታት በኋላ በደማስቆ መንገድ ላይ “በጸጋው” እንደጠራው ይናገራል (ገላትያ 1፥15)። ይህም ማለት በውልደቱ እና በደማስቆ መንገድ በመጠራቱ መካከል፣ ጳውሎስ – የተመረጠ፣ ነገር ግን ገና ያልተጠራ የእግዚአብሔር መጠቀሚያ ዕቃ ነበር ማለት ነው (ሐዋሪያት 9፥1522፥14)።

ይህ ማለት ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ይደበድብ፣ ያስር እና ይገድል የነበረው በእግዚአብሔር እንደተመረጠ፣ በቅርቡም የክርስቲያን ሚሲዎናዊ እንድሚደረግ ሰው ነበር ማለት ነው።

ስንጓዝም እኩለ ቀን ገደማ ወደ ደማስቆ እንደ ተቃረብሁ፣ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤ እኔም ምድር ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም “ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳደደኛለህ?” የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። (ሐዋሪያት 22፥6-7)

ለመካድም ሆነ ለማምለጥ የሚቻል አልነበረም። ከመወለዱ በፊት እግዚአብሔር አስቀድሞ ለዚህ መርጦታል። አሁን ደግሞ ይፈጽመዋል። የክርስቶስ ቃል ሉዓላዊ ነበር። ድርድር አልነበረውም።

“ተነስተህ ወደ ደማስቆ ሂድ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ሁሉ ይነግሩሃል።” (ሐዋሪያት 22፥10)

የደማስቆ ተዓምር ለብዙ አስርተ-ዓመታት ከባከነ መለኮታዊ የማዳን ጥረት በኃላ፣ ጳውሎስ በነጻ ፈቃዱ ራሱን ለክርስቶስ በመስጠቱ ምክንያት የተፈጸመ አልነበረም። እግዚአብሔር እርሱን የመረጠበት ጊዜ ነበረው — ያም ደግሞ ከመወለዱ በፊት ነው። እንዲሁም የጠራበት ጊዜ ነበረው — እርሱም በደማስቆ መንገድ ላይ ነው። እግዚአብሔር ጠራው፣ ጥሪውም የጳውሎስን መሰጠት ወለደ።

ስለዚህ፣ በጳውሎስ መወለድ እና መጠራት መካከል እግዚአብሔር እንዲደረጉ የፈቀዳቸው ኃጢአቶች፣ የዚህ ዕቅድ አካል ነበሩ ማለት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያ እንዲሆን ባይወድ ኖሮ አስቀድሞ ሊጠራው ይችል ነበር።

ለእነዚያ ኃጢአቶች ምን ታቅዶ እንደነበር ማወቅ እንችል ይሆን? እንችላለን። የተፈቀዱት ምናልባትም የኃጢአታችን ብዛት ከጸጋ ውጪ ያደርገናል ብለን ለምንፈራው — ለእናንተ እና ለእኔ ሲባል ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ የራሱን ኃጢአቶች ከተስፋችን ጋር የሚያዛምድበትን መንገድ ተመልከቱ፦

ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና አመጸኛ የነበርሁ ብሆንም፣ … ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግስቱን ከኃጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ። (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥13-16)

ልበ ደንዳና ብሎም ተስፋ ቢስ ለሆኑ ኃጢአተኞች፣ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ የማዳን ዕቅድ አቤት እንዴት ውብ ነው!