የመስቀሉ ድል አድራጊ ውርደት | ሕዳር 23

ሊቀ ካህናት የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ክርስቶስ ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሰማይ አልገባም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል። (ዕብራውያን 9፥​25–26)

በመንግሥተ ሰማያት ለኅጢአተኞች አቀባበል መደረጉ እንደ ቀላል ነገር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።

እግዚአብሔር ቅዱስና ንጹሕ፣ ፍጹምና ልክ፣ ጻድቅም ነው። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ታሪክ የሚተርከው፣ እንደዚህ ያለ ታላቅ እና ቅዱስ አምላክ እንደ እናንተና እንደ እኔ ያሉ ቆሻሻዎችን እና ርኩስ ሰዎችን እንዴት ሊቀበል እንደቻለ እና እንደተቀበለም ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ዕብራውያን 9፥25 ሲናገር፣ ክርስቶስ ስለ ኃጢአት ያቀረበው መሥዋዕት እንደ አይሁዶች ሊቀ ካህናት መሥዋዕት አልነበረም ይላል። የሕዝቡን ኅጢአት ለማስተስረይ በየዓመቱ ወደ ተቀደሰው ስፍራ የእንስሳት መሥዋዕትን ይዘው ይገቡ ነበር። ነገር ግን፣ ክርስቶስ ወደ መንግሥተ ሰማያት የገባው “ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ … ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር” (ዕብራውያን 9፥26)።

ክርስቶስ የካህናቱን ምሳሌ ተከትሎ ቢሆን ኖሮ በየዓመቱ መሞት ነበረበት። ደግሞም የሚሸፈኑት ኅጢአቶች የአዳምንና የሔዋንን ኅጢአት ስለሚያጠቃልል፣ ኢየሱስ በየዓመቱ የሚሞተው ዓለም ከመፈጠሩ ጀምሮ መሆን ነበረበት። ነገር ግን ጸሐፊው ይህንን የማይታሰብ አድርጎ ይመለከተዋል።

ለምንድን ነው ይህ የማይታሰብ የሆነው? ምክንያቱም፣ የእግዚአብሔር ልጅን ሞት ደካማ እና አጥጋቢ ያልሆነ እንዲመስል ያደርገዋል። ለዘመናት፣ ከዓመት ዓመት መደጋገም ካለበት፣ ድሉ የቱ ጋር ነው? ዋጋው የማይተመነውን የእግዚአብሔር ልጅ መሥዋዕትነት ምኑ ላይ ነበር የምናየው? በመከራው እና በሞቱ የድግግሞሽ ስቃይ ውስጥ ይሰወርብን ነበር።

በመስቀሉ ላይ ውርደት ነበር፤ ነገር ግን የድል አድራጊ ውርደት ነበር። “የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” (ዕብራውያን 12፥2)።

ይህ የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነው የክርስቶስ የክብር ወንጌል ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4)። ከኅጢአታችሁ የተነሳ ምንም ያህል የቆሸሻችሁ ወይም ርኩስ ብትሆኑም፣ የዚህን ክብር ብርሃን እንድታዩና እንድታምኑ እጸልያለሁ።