የልብ መስኮት | ጥር 14

እንግዲህ ዝላችሁ ተስፋ እንዳትቈርጡ፣ ከኃጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን ዐስቡ። (ዕብራውያን 12፥3)

ከሰው አዕምሮ አስገራሚ ባህርያት መካከል አንዱ፣ ትኩረቱን ወደ መረጠው ነገር ማድረግ መቻሉ ነው። ቆም በማለት ለአዕምሯችን “ይህን አስብ፣ ያንን ደግሞ አታስብ” ማለት እንችላለን። ትኩረታችንን ወደ ፈለግነው ሀሳብ ወይም ምስል ወይም ችግር ወይም ተስፋ ማድረግ እንችላለን።

ይህ አስደናቂ ኀይል ነው። እንስሳት ይህ ክሕሎት ያላቸው መሆኑን እጠራጠራለሁ። ራሳቸውን የሚያውቁ እና ወደ ውስጣቸው የሚመለከቱ አይመስለኝም፤ ይልቁንም በደመ ነፍስ እና በስሜት የሚመሩ ናቸው።

ከኃጢአት ጋር በምታደርጉት ፍልሚያ ይህንን ታላቅ መሳሪያ ችላ ብላችሁት ይሆን ብዬ አስባለሁ። ይህንን አስገራሚ ስጦታ እንድንጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ ይነግረናል። ይህንን ስጦታ ከተቀመጠበት መደርደሪያ ላይ አንስተንና የሸፈነውን አቧራ አራግፈንለት፣ እንጠቀመው።

ለምሳሌ ጳውሎስ በሮሜ 8፥5-6 እንዲህ ይላል፦ “እንደ ሥጋ የሚኖሩ ልባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ልባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ህይወትና ሰላም ነው”።

ይህ አስገራሚ ነው። ሀሳባችንን የምናኖርበት ቦታ ነገሩ የህይወት ወይም የሞት ጉዳይ መሆኑን ይወስናል።

አብዛኞቻችን ለለውጥ፣ ሙሉነትንና ሰላምን ለመፈለግ የማንተጋ ሆነናል። በዚህ ስነ-ልቦናዊ ውይይት በተስፋፋበት ጊዜ ላይ በመኖራችን ትኩረታችን ሁሉ፣ “ችግሮቻችን መነጋገር እና መቀበል ላይ” አልያም ደግሞ፣  “የችግቻችንን ሥር አስተዳደጋችን ውስጥ መፈለግ ላይ” ብቻ እንዳደረግን ይሰማኛል።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ግን የበለጠ ቆራጥ የሆነና በቀጥታ ችግሩን ከመጋፈጥ ጋር ያለ ለውጥ አፈላለግ አያለሁ። ቈላስይስ 3፥2 እንዲህ ይላል፦ “አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን”።

ስሜቶቻችን በዋነኝነት በምናስባቸውና በምናሰላስላቸው ነገሮች ይመራሉ። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ጭንቀታችንን ለማሸነፍ ምን ማሰላሰል እንዳለብን ነግሮናል፦ “ቁራዎችን ተመልከቱ … አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ” (ሉቃስ 12፥2427)።

አእምሮ የልብ መስኮት ነው። አእምሯችን ጨለማ ነገሮችን ያለማቋረጥ እንዲያስብ ከፈቀድንለት፣ ልባችንም ጨለማ የሆነ ስሜት ውስጥ ይገባል። የሀሳባችንን መስኮት ለብርሃን ከከፈትን ደግሞ፣ ልባችንም አብሮ ይፈካል።

ከምንም በላይ ግን፣ የአእምሮአችን የማስተዋልና የማሰላሰል ኀይል የተሰጠን፣ ኢየሱስን እንድናስብብት ነው (ዕብራውያን 12፥3)። ስለዚህም “ዝላችሁ ተስፋ እንዳትቈርጡ፣ ከኃጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን ዐስቡ።”