የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።
ሮሜ 5፥10-11
ዕርቅን ተቀብለን በእግዚአብሔር ልንመካ የምንችለው እንዴት ነው? ይህንን ልናደርግ የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። ይህ ማለት በአዲስ ኪዳን በሥራው እና በንግግሩ የተገለጸውን የኢየሱስን ማንነት በእግዚአብሔር የምንደሰትበት ዋነኛው ነገር እናደርገዋለን ማለት ነው። በአዲስ ኪዳን በማንነቱ እና በሥራው በተገለጠው ኢየሱስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ሐሴት እናደርጋለን። ክርስቶስን ማዕከላዊ ሳናደርግ በእግዚአብሔር ለመደሰት ብንሞክር ክርስቶስን ሳናከብር እንቀራለን። ክርስቶስ ባልከበረበት ደግሞ እግዚአብሔርም አይከብርም።
በ 2 ቆሮንቶስ 4፥4-6 ጳውሎስ በክርስቶስ መለወጥን በሁለት መንገድ ይገልጸዋል። በቁጥር 4 መሠረት የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነውን የክርስቶስን ክብር መመልከት ነው። ቁጥር 6 ላይ ደግሞ በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን ክብር መመልከት እንደሆነ ይነግረናል። በሁለቱም መንገድ ዋና ሐሳቡ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው። የእግዚአብሔር መልክ የሆነው ክርስቶስ አለን፤ ከዚያ ደግሞ በክርስቶስ መልክ ውስጥ እግዚአብሔር አለን።
በእግዚአብሔር ሐሴት የምናደርገው በክርስቶስ ኢየሱስ መልክ ውስጥ በምናየው እና በምናውቀው እግዚአብሔር ሐሴት በማድረግ ነው። ይህን ደግሞ በሙላት ልንለማመድ የምንችለው የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ሲፈስ እንደሆነ ሮሜ 5፥5 ይነግረናል። ያ ጣፋጭ የሆነ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የተገኘ የእግዚአብሔር ፍቅር የቁጥር 6ን ታሪካዊ እውነተኝነት ስናሰላስል ለእኛ ደግሞ ተግባራዊ ይሆናል። “ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና” (ሮሜ 5፥6)።
የገና ዋና ነጥቡ ይህ ነው። እግዚአብሔር በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርቅን ገዛልን ብቻ አይደለም (ሮሜ 5፥10)። እንደገናም ደግሞ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ዕርቅ ማግኘት እንድንችል አደረገን ብቻም አይደለም። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ፣ አሁን ላይ ሆነን በመንፈስ ቅዱስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በራሱ በእግዚአብሔር ሐሤት ማድረግ ሆኖልናል!
ኢየሱስ ዕርቅን ገዝቶልናል። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅን አስገኝቶልናል፤ በእርሱ አማካኝነት ስጦታውን መክፈት ሆኖልናል። አምላክ የሆነው ኢየሱስ ራሱ ሥጋ ለብሶ፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ስጦታ ሆኖ በፊታችን በመቅረብ፣ በእግዚአብሔር መደሰት እንችል ዘንድ ልባችንን ያቀጣጥላል።
በዚህ ገና ወደ ኢየሱስ ተመልከቱ። በደሙ የገዛውን ዕርቅ ተቀበሉ። የሰጣችሁን ስጦታ እንደታሸገ መደርደሪያ ላይ አታስቀምጡት። ስትከፍቱት ደግሞ በውስጡ ያለው ስጦታ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያችን የሆነው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አስታውሱ።
በእርሱ ሐሤት አድርጉ። የእርካታችሁ ምንጭ ይሁን። ውዱ ሀብታችሁ አድርጉት።