ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ መልካም ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥11)።
ጳውሎስ እግዚአብሔር መልካም የማድረግ ፍላጎታችሁን በእምነት በኩል በኅይሉ ይፈጽማል ሲል፤ ኃጢአትን አሸንፈን ጽድቅን በእምነት እናደርጋለን ማለቱ ነው። ይህም የሚሆነው በሚቀጥሉት አምስት ደቂቃዎች፣ አምስት ሳምንታት፣ አምስት ወራት፣ ወይም አምስት አስርት ዓመታት፣ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በክርስቶስ ለእኛ እንደሚሆንልን በሰጠን ተስፋ ሁሉ በመርካት ነው።
ይህ በሕይወታችሁ ውስጥ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
1. በመስዋዕትነትና በልግስና ለመስጠት ልባችሁን ብታዘጋጁ፣ ይህንን መልካም ምኞት ለማሳካት የሚረዳችሁ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የወደፊት ጸጋውንና የገባላችሁን ቃል በምትታመኑበት ጊዜ ወደ እናንተ ይመጣል። የገባላችሁን ቃል ኪዳኖች አስታውሱ፦
“አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል” (ፊልጵስዩስ 4፥19)።
“ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል” (2ኛ ቆሮንቶስ 9፥6)።
“ሁል ጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” (2ኛ ቆሮንቶስ 9፥8)።
በእነዚህ ተስፋዎች ውስጥ ያለውን የእርሱን የወደፊት ጸጋ ስታምኑ፣ ይህን መልካም የማድረግ ምኞታችሁን ለመፈጸም የእግዚአብሔር ኀይል ወደ እናንተ ይመጣል።
- የፖርኖግራፊን ኀጢአት ለመተው ልባችሁን ብታዘጋጁ፣ ይህንን መልካም ምኞት ለማሳካት የሚረዳችሁ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የወደፊት ጸጋውንና የገባላችሁን ቃል በምትታመኑበት ጊዜ ወደ እናንተ ይመጣል። ቃል ኪዳኖቹ እነዚህ ናቸው፦ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” ብሏል (ማቴዎስ 5፥8)። “ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል” (ማቴዎስ 5፥29)። በጣም ይሻላል። እጅግ በጣም ይሻላል። ከምንም ነገር በላይ ከገሃነም አምልጠን መንግስተ ሰማይ መግባት ይሻላል።
- ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ክርስቶስ ለመናገር ልባችሁን ብታዘጋጁ፣ ይህንን መልካም ምኞት ለማሳካት የሚረዳችሁ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የወደፊት ጸጋውንና የገባላችሁን ቃል በምትታመኑበት ጊዜ ወደ እናንተ ይመጣል። የገባላችሁ ቃል እነሆ፦ “በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል” (ማቴዎስ 10፥19)። በእርግጥም፣ ያለ አንዳች ጥርጥር፣ በዚህ ተስፋ የወደፊቱን ጸጋ ስታምኑ መልካም የማድረግ ምኞታችሁን ለመፈጸም የእግዚአብሔር ኀይል ወደ እናንተ ይመጣል።
እግዚአብሔር ወሰን በሌለው፣ በደም በተገዛውና ክርስቶስን በሚያከብረው የወደፊት ጸጋው ላይ የዘወትር እምነታችንን ይጨምር።