ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ … ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።
1ኛ ዮሐንስ 2፥1-2፣ 3፥7-8
ይህንን አስደናቂ ሁኔታ ከእኔ ጋር አብራችሁ አሰላስሉ። የእግዚአብሔር ልጅ የመጣው ኀጢአት መሥራት እንድታቆሙ ሊረዳችሁ፣ የዲያቢሎስን ሥራ ሊያፈርስ፣ እና ኀጢአት ስትሠሩ ደግሞ ሊያስተሰርይላችሁና የእግዚአብሔርን ቁጣ ከላያችሁ ሊያነሣ ከሆነ፣ ይህ እውነት ሕይወታችሁን ለመኖር ምን ዐይነት አንድምታ ይኖረዋል? ምንስ ይሰጠናል?
በጣም ግሩም የሆኑ ሦስት ነገሮች ይሰጠናል። እነዚህን ደግሞ በአጭሩ ለእናንተ የገና ስጦታ እንዲሆን ልሰጣችሁ እወዳለሁ።
ስጦታ 1፦ ለኑሯችን ግልጽ የሆነ ዓላማ
የመጀመሪያው አንድምታ ለምንኖረው ሕይወት ግልጽ የሆነ ዓላማ መስጠቱ ነው። የዚህ አሉታዊ ትርጉሙ በቀላሉ ሲታይ፦ ኀጢአት አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያከብር ነገር አታድርጉ ነው። “ልጆቼ ሆይ፤ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህንን እጽፍላችኋለሁ” (1ኛ ዮሐንስ 2፥1)። “የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው” (1ኛ ዮሐንስ 3፥8)።
ይህንን ዓረፍተ ነገር አዎንታዊ በሆነ መንገድ ንገረን ካላችሁኝ መልሴ የሚሆነው በ1ኛ ዮሐንስ 3፥23 ተጠቅልሎ የተቀመጠው ነው። የዮሐንስ ሙሉ መልእክት የያዘውን ሐሳብ ምርጥ በሆነ መንገድ የሚጠቀልል ጥቅስ ነው። በነጠላ ቁጥር የተቀመጠችውን “ትእዛዚቱን” የምትለዋን ቃል ልብ በሉ፦ “ ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ”። እነዚህ ሁለት ነገሮች በጣም ከመያያዛቸው የተነሣ ዮሐንስ እንደ አንድ ትዕዛዝ አድርጓቸዋል፦ በኢየሱስ እመኑ እና ሌሎችን ውደዱ። ያ ነው ዓላማችሁ። የክርስትና ሕይወት ሲጨመቅ ያ ነው። በኢየሱስን መታመን፣ እና ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ ባስተማሩን መንገድ ሰዎችን መውደድ። ኢየሱስን ማመን፣ ሰዎችን መውደድ። ያ ነው የመጀመሪያው ስጦታ፦ ለመኖራችን ዓላማ።
ስጦታ 2፦ ውድቀቶቻችን ሁሉ ይቅር እንደሚባሉ የሚያረጋግጥ ተስፋ
ኢየሱስ ኀጢአተኝነታችንን ለመደምሰስ እና ይቅር ለማለት ከመምጣቱ የምናገኘው ሁለተኛው አንድምታ ይህ ነው፦ ውድቀቶቻችን ይቅር እንደሚባሉ ተስፋ ሲኖረን፣ ኀጢአታችንን ለማሸነፍ የተሻለ አቅም ይኖረናል። እግዚአብሔር ውድቀቶቻችሁን ይቅር እንደሚል ተስፋ ካላደረጋችሁ፣ ኀጢአትን መዋጋት ገና ስትጀምሩ ተስፋ ትቆርጣላችሁ።
አንዳንዶቻችሁ በዚህ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ወቅት ለማምጣት የምትፈልጉት ለውጥ ይኖራል። ምናልባት የኀጢአት ልምምድ ውስጥ ገብታችሁ ከዚያ ለመውጣት ትግል ላይ ትሆኑ ይሆናል። ምናልባት አዲስ የአመጋገብ ልምድ፣ ወይም ደግሞ የተለየ ዐይነት መዝናኛ ትፈልጉ ይሆናል። አንዳንዶቻችሁ ደግሞ የማካፈል እና የመስጠት ልምዳችሁን ለማዳበር ትፈልጉ ይሆናል። ሌሎቻችሁ ደግሞ ከትዳር አጋራችሁ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ወይም የቤተሰብ ጸሎት ፕሮግራማችሁን ማስተካከል ትፈልጉ ይሆናል። ለአንዳንዶቻችሁ ደግሞ የእንቅልፍ እና የስፖርት ጊዜያችሁን መቀያየር ትፈልጉ ይሆናል። የሌሎች ፍላጎት ደግሞ ወንጌል በመስበክ መትጋት ይሆናል። ነገር ግን “ይህ ሁሉ ምን ጥቅም ይኖረዋል?” በሚል ግራ መጋባት ውስጥ ትሆናላችሁ። እነሆ፤ ሁለተኛው የገና ስጦታችሁ፦ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው የዲያቢሎስን ሥራ፣ ማለትም የእኛን ኀጢአተኝነት ሊያፈርስ ብቻ ሳይሆን፣ ለውድቀቶቻችን ሊከራከርልን እና ጠበቃ ሊሆንልን ጭምር ነው።
ስለዚህም፣ ውድቀት እስከመጨረሻው እንደማይሰለጥንባችሁ በማወቅ ለትግል ተስፋ እንድትሰንቁ እማፀናችኋለሁ። ነገር ግን ተጠንቀቁ! የእግዚአብሔርን ጸጋ ለኀጢአት ፈቃድ አድርጋችሁ በመውሰድ፣ “ውድቀቴ ብዙም ለውጥ ከሌለው፣ ከኀጢአት ጋር ምን አታገለኝ?” የምትሉ ከሆነ እና በርግጥም አምርራችሁ በዚያ መንገድ የምትቀጥሉ ከሆነ፣ መዳናችሁ እጅግ አጠራጣሪ ነውና ልትደንግጡ ይገባል።
ሆኖም ግን አብዛኞቻችሁ ያላችሁት እንደዛ ዐይነት አስተሳሰብ ውስጥ አይደለም። ብዙዎቻችሁ በሕይወታችሁ ያለውን የኀጢአት ልምምድ ለማሸነፍ ትፈልጋላችሁ። እግዚአብሔር ለእናንተ የሚላችሁ ይህንን ነው፦ ክርስቶስ ውድቀታችሁን ሸፍኗልና ከኀጢአት ጋር ለመዋጋት ተስፋ ሰንቁ። “ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”
ስጦታ 3፦ ክርስቶስ ያግዘናል
በመጨረሻ፣ ኢየሱስ የመጣው ኀጢአት መሥራታችንን ሊያሸንፍ እና ይቅር ሊለን መሆኑ የሚያስከትለው ሦስተኛው አንድምታ ይህ ነው፦ ክርስቶስ በርግጥም በፍልሚያችን ውስጥ ያግዘናል። በእውነት ይረዳሃል፤ ይረዳሻል። ከጎናችሁ ነው። ኀጢአት ቀልድ ቢሆን ኖሮ ሊደመስሰው ባልመጣ ነበር። ኀጢአትን ሊደመስስ የመጣው አደገኛ እና ነፍሰ በላ ስለሆነ ነው። ኅጢአት የሰይጣን ማታለያ ሲሆን ካልተፋለምነው ያጠፋናል። ክርስቶስ የመጣው በዚህ ፍልሚያ ውስጥ ሊያግዘን እንጂ ሊጎዳን አይደለም።
ስለዚህም ሦስተኛው የገና ስጦታችሁ ይኸውና፦ በውስጣችሁ ያለውን ኀጢአት ለማሸነፍ ክርስቶስ ያግዛችኋል። 1ኛ ዮሐንስ 4፥4 “በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና” ይላል። ኢየሱስ ሕያው ነው፤ ኢየሱስ ኀያል ነው፤ ኢየሱስ በእምነት በውስጣችን ይኖራል። ኢየሱስ ደግሞ የእኛ ወገን እንጂ ተቃዋሚያችን አይደለም። በዚህ በአዲሱ ዓመት ከኀጢአት ጋር በሚኖራችሁ ትንቅንቅ እርሱ ያግዛችኋል። ታመኑት።