እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል። ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ። (ኤፌሶን 5፥24-25)
በእግዚአብሔር ተወስኖ የተቀረጸ ትዳር ውስጥ የፍቅር ንድፍ አለ።
የባል እና የሚስት የሥራ ድርሻዎች ተመሳሳይ አይደሉም። ባል ልዩ የሆኑ ኅላፊነቶቹን ከክርስቶስ መውሰድ አለበት፤ ሚስት ደግሞ ለክርስቶስ ተገዢ ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን የራሷን መገለጫዎች መውሰድ አለባት።
ይህንን ስናደርግ በኅጢአት የተሞሉት የውድቀት ውጤቶች መቀልበስ ይጀምራሉ። ውድቀት የሰው ልጅን በፍቅር የተሞላው ገዢነቱን ወደ ጨቋኝነት ወይም ወደ ስንፍና ቀይሮት ነበር። በተጨማሪም፣ ይህ ውድቀት የሴትን ልጅ ብልህ ታዛዥነት ወደ ተንኮለኝነት እና ወደ አለመታዘዝ ጭምር ቀይሮት ነበር።
መሲሑ ክርስቶስ ሲመጣ የጠበቅነው ለውጥ የዚህን (በፍቅር መግዛት እና በደስታ መታዘዝ) ስርዐት መፍረስ ሳይሆን፣ መጠገኑን እና መስተካከሉን ነበር። ሚስቶች የተበላሸ ታዛዥነታችሁን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ሐሳብ በማየት አስተካክሉ፤ ባሎች ደግሞ የተኮላሸውን መሪነታችሁን እግዚአብሔር ለልጁ ክርስቶስ ያሰበውን በማየት አስተካክሉ።
በኤፌሶን 5፥21-33 ላይ ሁለት ነገሮች ታገኛላችሁ፦
1) በጋብቻ ውስጥ ያለ ክርስቲያናዊ ፍቅር ምን እንደሚመስል ሲሆን
2) ምን ዐይነት አቅጣጫ መያዝ እንዳለበት እናገኛለን።
ሚስቶች ሆይ! ባላችሁ በእግዚአብሔር የተሰጠውን የራስነት ሚና በማክበር በእርሱ ደስታ ውስጥ የራሳችሁን ደስ መሰኘት ፈልጉ። ባሎች ደግሞ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ ያለባችሁን ኅላፊነት በመቀበል በዚህ ውስጥ ደስታችሁን ፈልጉ።
ስለ እግዚአብሔር መልካምነት ራሴ ልመሰክር እወዳለሁ። ክርስቲያናዊ ፍቅር የገባኝ ጋብቻ በፈጸምኩበት ዓመት፣ እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም. ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኖኤል እና እኔ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመታዘዝ በቻልነው አቅም ሁሉ በአንዳችን ደስታ ውስጥ የራሳችንን ደስታ ለማግኘት እየጣርን ነው።
እናም ከ50 ዓመት የትዳር ቆይታ በኋላ ላላገቡ ሰዎች ይህ ብቸኛው መንገድ መሆኑን መመስከር እንችላለን። እኛ በሌላችን ደስታ ውስጥ የራሳችንን መደሰት በፈለግን ቁጥር፣ እግዚአብሔር እንዲገለጥልን የሚፈልገውን የክርስቶስ እና የቤተ ክርስቲያን ግንኙነት ምስጢር እያገኘነው እንመጣለን። እርሱም በዚህ ይከብራል።