ትክክለኛ እውቀት ታላቅ ደስታን ያመጣል | ግንቦት 7

ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ከምግባቸው ከፍለው ለመላክና ሐሤትም ለማድረግ ሄዱ። (ነህምያ 8፥12)

የእግዚአብሔርን እውነተኛ ማንነት የሚገልጥ፣ ደግሞም እርሱን በሚያከብር ፍቅር የተሞላ ብቸኛ ደስታ፣ እውነተኛ በሆነ በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የተመሰረተ ደስታ ነው። ታዲያማ የእኛ እውቀት አናሳና ስሕተት የተሞላ በሆነ ቁጥር፣ ደስታችንም የእግዚአብሔርን ታላቅነት በትክክል የሚገልጽ አይሆንም።

ነህምያ 8፥12 ላይ፣ እስራኤላውያን ደስ የተሰኙበት መንገድ፣ እውነተኛ የሆነውና እግዚአብሔርን የሚያከብረው ደስታ እንዴት ከልብ እንደሚመነጭ ያሳየናል። ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል አነበበላቸው። ቀጥለውም ሌዋውያኑ አብራሩላቸው። ሕዝቡም “የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ከምግባቸው ከፍለው ለመላክና ሐሤትም ለማድረግ ሄዱ።”

የተደሰቱት፣ ሐሤትን ያደረጉት እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ስለተረዱ ነበር።

አብዛኞቻችን ይህንን ልብ የሚያቀልጥ ደስታ የእግዚብሔር ቃል በበራልን ጊዜ ቀምሰነዋል (ሉቃስ 24፥32)። ሁለት ጊዜም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የሚያስተምራቸው ለደስታቸው ሲል እንደሆነ ነግሯቸዋል።

  • ዮሐንስ 15፥11፦ “ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ።”
  • ዮሐንስ 17፥13፦ “ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ።”

ከሁሉም በላይ፣ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የምናየው ዋነኛ ነገር፣ ራሱን እግዚአብሔርን ነው። እንድናየው፣ እንድናውቀው እና ደስ እንድንሰኝበት ራሱን በቃሉ ውስጥ ገልጦልናል። “እግዚአብሔር በሴሎ ይገለጥ ነበር፤ በዚያም በቃሉ አማካይነት ራሱን ለሳሙኤል ገለጠ” (1ኛ ሳሙኤል 3፥21)።

እዚህ ጋር ዋናው ነጥብ፣ ደስታችን የእግዚአብሔርን ክብር እንዲያንጸባርቅ የምንፈልግ ከሆነ፣ ይህን የምናደርገው ግርማውን እና ክብሩን በእውነት በማወቅ መሆኑን መረዳት አለብን። በእግዚአብሔር በሚገባ ደስ ለመሰኘት፣ በሚገባ ልናውቀው ግድ ይለናል።