የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ፤ ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’። (ኢሳይያስ 46፥10)
“ሉዓላዊ” የሚለው ቃል (ልክ “ሥላሴ” እንደሚለው ቃል) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። እግዚአብሔር ከትልልቅ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጀምሮ በጫካ ውስጥ እስካለችው ትንሽ ወፍ ድረስ፣ የምድርን ነገሮች ሁሉ እንደሚቆጣጠር ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ “እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም… ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’“ (ኢሳይያስ 46፥9-10)። “የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይ ኀይላት፣ በምድርም ሕዝቦች ላይ፣ የወደደውን ያደርጋል፤ እጁን መከልከል የሚችል የለም፤ ‘ምን ታደርጋለህ?’ ብሎ የሚጠይቀውም የለም“ (ዳንኤል 4፥35)። “እርሱ ግን ራሱን ችሎ ብቻውን የሚኖር ነው፤ የሚቋቋመውስ ማን ነው፤ እርሱ የፈቀደውን ያደርጋል። በእኔ ላይ የወሰነውን ይፈጽማል፤ ይህን የመሰለ ዕቅድም ገና ብዙ አለው“ (ኢዮብ 23፥13-14)። “አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል“ (መዝሙር 115፥3)።
ይህ አስተምህሮ ለአማኞች እጅግ ውድ የሆነበት ምክንያት የእግዚአብሔር ትልቁ ፍላጎት ለሚያምኑት ምሕረት እና መልካምነት ማሳየት እንደሆነ ስለምናውቅ ነው (ኤፌሶን 2፥7፤ መዝሙር 37፥3-7፤ ምሳሌ 29፥25)። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው ማለት ለእኛ ያለው ዕቅድ ሊቆም ወይም ሊፈርስ አይችልም ማለት ነው።
የሚወዱትና እንደ ሐሳቡ የተጠሩት በፍፁም ክፉ አይነካቸውም፤ ይልቅ መልካም ሁሉ ይሆንላቸዋል (ሮሜ 8፥28፤ መዝሙር 84፥11)።
ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት እና ምሕረት የሕይወቴ ሁለት ምሰሶዎች ናቸው የምለው። የወደ ፊቴ ተስፋ፣ የአገልግሎቴ ኅይል፣ የእምነቴ መሠረት፣ የጋብቻዬ ሰንሰለት፣ የሕመሜ መድሐኒት እና የተስፋ መቁረጤ ሁሉ መፍትሔ ናቸው።
ደግሞም ወደ ፊት ልሞት ስቃረብ እነዚህ ሁለት ጠንካራ እና የማይሰበሩ እውነታዎች ከአልጋዬ ጎን ቆመው ወደ እግዚአብሔር እጆች ያነሡኛል።