ለኢየሱስ ሁለት ዐይነት ተቃውሞዎች | ታሕሳስ 13

ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች።

የማቴዎስ ወንጌል 2፥3 (አ.መ.ት)

ኢየሱስን ሊያመልኩ የማይፈልጉ ሰዎች በእርሱ ይታወካሉ፤ ሊያመልኩት በወደዱ ላይ ደግሞ ተቃውሞ ያስነሣባቸዋል። ምናልባት የማቴዎስ ዋነኛ ነጥብ ይህ ሐሳብ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ታሪኩ ሲቀጥል ልናመልጠው የማንችለው ወሳኝ አንድምታ ነው።

በዚህ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስን ማምለክ የማይፈልጉ ሁለት ዐይነት ሰዎች አሉ።

የመጀመሪያው ዐይነት ስለ ኢየሱስ ምንም ግድ የማይሰጣቸው እና ምንም የማያደርጉ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ በሕይወታቸው ምንም ሚና የለውም። የካህናት አለቆች እና ጻፎች ይህንን ቡድን በኢየሱስ ሕይወት መጀመሪያ ሰሞን ወክለው ይገኛሉ። ማቴዎስ 2፥4 እንዲህ ይላል፦ “[ሄሮድስም] የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው።” እነርሱም ነገሩት፤ ከዚያ ግድም ሳይሰጣቸው ወደተለመደው ኑሯቸው ተመለሱ። እነዚህ መሪዎች ከክስተቱ ግዝፈት እና ወሳኝነት አንፃር ሲታይ፣ በጉዳዩ ላይ ያላቸው ዝምታ እና ግድ የለሽነት ያስጨንቃል።

ከዚያ ደግሞ ማቴዎስ 2፥3 የሚለውን አስተውሉ፦ “ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች”። በሌላ አነጋገር፣ መላው የኢየሩሳሌም ከተማ በመሲሕ መወለድ ወሬ ታምሶ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የካህናት አለቆች ዝምታ አስደንጋጭ ነው። ወደ ሰብዓ ሰገል ለመሄድ ለምን ጥረት አላደረጉም? ፍላጎቱም ሆነ ተነሣሽነቱ የላቸውም። የእግዚአብሔርን ልጅ የማግኘት እና የማምለክ ጥማት አይታይባቸውም።

ኢየሱስን ማምለክ የማይፈልጉት ሁለተኞቹ ዐይነት ሰዎች ደግሞ በኢየሱስ ጥልቅ የሆነ ሥጋት ያደረባቸው ሰዎች ናቸው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ሄሮድስ ይህንን ጎራ ይወክላል። ሄሮድስ እጅግ ፈርቷል፤ ከፍርሃቱም ጥልቀት የተነሣ ይዋሻል፤ ያጭበረብራል፤ ከዚያም አልፎ ኢየሱስን ለማጥፋት ሲል የጅምላ ጭፍጨፋ ያውጃል።

ዛሬም ላይ እነዚህ ሁለት ዐይነት ተቃውሞዎች በክርስቶስ እና እርሱን በሚያመልኩት ሁሉ ላይ ይከሰታሉ። ግድ የለሽነት እና ጠላትነት። ከሁለቱም ጎራዎች እንደማትሰለፉ ከልቤ ተስፋ አደርጋለሁ።

ክርስቲያን ከሆናችሁ ደግሞ ይህ የገና በዓል መሲሑን መከተል እና ማምለክ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ምንኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል የምታሰላስሉበት ወቅት እንዲሆንላችሁ እጓጓለሁ።