የገና ሁለት ዓላማዎች | ታሕሳስ 28

ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኀጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው። ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ ኀጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው።

1ኛ ዮሐንስ 3፥7-8 (አ.መ.ት)

1ኛ ዮሐንስ 3፥8የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው” ሲል ስለ የትኛው የዲያቢሎስ ሥራ እያወራ ነው ያለው? መልሱ ከአውዱ ግልጽ ነው።

በመጀመሪያ፣ 1ኛ ዮሐንስ 3፥5 ግልጽ የሆነ ማስተያያ ነው። “እርሱ ኀጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ።” እንደ ተገለጠ የሚለው ሐረግ ቁጥር 5 እና 8 ላይ ተጠቅሶ ታገኛላችሁ። ስለዚህ ኢየሱስ ሊያፈርስ የተገለጠው “የዲያቢሎስ ሥራ” ኀጢአቶችን ነው ልንል እንችላለን። የቁጥር 8 የመጀመሪያው ክፍል ይህንን ግልጽ ያደርገዋል። “ኀጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው። ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ ኀጢአትን የሚያደርግ ነው።”

በዚህ ዐውድ መሠረት ዋናው ችግር በሽታ፣ የተበላሸ መኪና፣ ወይም የተመሰቃቀለ ሕይወት ሳይሆን ኀጢአትን ማድረግ ነው። ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው ኀጢአት መሥራት ማቆም እንችል ዘንድ ነው።

ይህ እውነት ደግሞ በይበልጥ ጎልቶ የምናየው ከ1ኛ ዮሐንስ 2፥1 ጎን ለጎን ስናነበው ነው፤ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ።” የገና በዓል፣ የኢየሱስ ሰው ሆኖ መወለድ፣ አንዱ እና ዋነኛው ዓላማ ይህ ነው (1ኛ ዮሐንስ 3፥8)።

እዚህ ዓላማ ላይ ደግሞ ዮሐንስ የሚጨምረው ሌላ ዓላማ አለ። “…ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” (1ኛ ዮሐንስ 2፥1-2)።

አሁን ይህ ምን ማለት እንደሆነ ልብ በሉ። ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው ለሁለት ምክንያት ነው ማለት ነው። አንደኛው ምክንያት ኀጢአት እያደረግን እንዳንቀጥል የዲያቢሎስን ሥራ ሊያፈርስ ሲሆን (1ኛ ዮሐንስ 3፥8)፣ ሁለተኛው ምክንያት ኀጢአት ከሠራን ደግሞ ለኀጢአታችን ማስተሰረያ ሊሆንልን ነው። በእኛ ላይ የነደደውን የእግዚአብሔርን ቁጣ በራሱ ላይ ጭኖ በምትካችን መሥዋዕት ሆኖ ሊያድነን መጥቷል።

የሁለተኛው ዓላማ ጥቅም ከመጀመሪያው ዓላማ ጋር አይጣረስም። የምሕረት ዓላማ ኀጢአትን መፍቀድ አይደለም። ኢየሱስ ለኀጢአታችን የሞተው ከኀጢአት ጋር ያለንን ጦርነት እንድናለሳልስ አይደለም። የእነዚህ ሁለት የገና ዓላማዎች ጥቅም ይህ ነው። ለኀጢአታችን አንድ ጊዜ የተደረገው ክፍያ ኀጢአትን ማሸነፍ የምንችልበትን ጉልበት እና ነጻነት ያጎናጽፈናል ማለት ነው። ይህንን ደግሞ የምናደርገው መዳናቸውን በሥራ ለማግኘት እንደሚፈልጉ ሕጋዊያን፣ ወይም ደግሞ መዳናችንን ልናጣ እንችላለን በሚል ፍርሃት ውስጥ እንደሚኖሩ ሰዎች አይደለም። ይልቁንም ሕይወታችንን ቢያስከፍለን እንኳን፣ ከኀጢአት ጋር ያለውን ጦርነት በድፍረት እና በደስታ እንደ አሸናፊዎች እንጋፈጣለን።