በገና የሚገኘው አንድነት | ታሕሳስ 24

የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያቢሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው።

1ኛ ዮሐንስ 3፥8

ሰይጣን በየቀኑ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኀጢአቶችን እያሰለፈ ይፈበርካል። በትልልቅ የጭነት አውሮፕላኖች እየጫነ ወደ መንግሥተ ሰማይ በመላክ በእግዚአብሔር ፊት ዘርግፎ ይስቃል፤ ያሽካካል።

አንዳንድ ሰዎች የዚህ ፋብሪካ ሰልፍ ቋሚ ቅጥረኞች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ሥራ መልቀቂያ አስገብተው አልፎ አልፎ ግን ይሠራሉ።

በዚህ ፋብሪካ በየደቂቃው የሚመረተው ምርት፣ እግዚአብሔርን የሰይጣን መሳለቂያ ያደርገዋል። የእግዚአብሔርን ብርሃን፣ ውበት፣ ንጽሕና እና ክብር አክርሮ የሚጠላው ሰይጣን፣ ኀጢአትን ዋነኛ ቢዝነሱ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። ፍጥረታት ፈጣሪያቸውን ሲንቁ፣ ሳይታዘዙ እና ሲጠራጠሩ እንደሚደሰተው በምንም አይደሰትም።

በዚህም ምክንያት ገና ለሰው ልጅ እና ለእግዚአብሔር መልካም ዜና ነው። “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው” (1 ጢሞቲዎስ 1፥15)። ይህ ለእኛ መልካም ዜና ነው። “የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያቢሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው” (1ኛ ዮሐንስ 3፥8)። ይህ ደግሞ ለእግዚአብሔርም መልካም ዜና ነው።

ገና ለእግዚአብሔር መልካም ዜና የሆነበት ምክንያት፣ ኢየሱስ የመጣው የሰይጣን ፋብሪካ ላይ የሠራተኞች አድማ ለመምራት ስለሆነ ነው። ፋብሪካ ውስጥ ገብቶ፣ ታማኝ ለሆኑት የአንድነት ጥሪ አቅርቦ፣ ከፍተኛ የሆነ የሰው ፍልሰት አስጀምሯል።

ገና የኀጢአት ፋብሪካ የሠራተኞች ሰልፍ ላይ የታወጀ የአድማ ጥሪ ነው። ከአመራሮች ጋር የሚደረግ ድርድር ወይም ስምምነት የለም። ሠራተኞች በግላቸው ወስነው፣ እዚህ እዛ ሳይሉ ለሚመረተው ምርት ያላቸውን ቀጥተኛ ተቃውሞ የሚገልጹበት አድማ ነው። ከእንግዲህ ይህንን ምርት አናመርትም።

የገና አንድነት የፋብሪካውን የጭነት አውሮፕላኖች በረራ ያሰርዛል። ያለ አንዳች ኀይል እና ሁከት ለእውነት ባለው የጸና ትጋት የሰይጣን ፋብሪካ ሕይወትን የሚያጠፋ መሆኑን ያጋልጣል።

የገና አንድነት ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ እስኪዘጋ ድረስ አያርፍም፤ ተስፋም አይቆርጥም።

ኀጢአት ድባቅ ተመትቶ ከምድረ ገጽ ሲጠፋ፣ ያኔ የእግዚአብሔር ስም ሙሉ በሙሉ ነጻ ይወጣል። ከእንግዲህ የሚስቅ፣ የሚሳለቅ አይኖርም። በዚህ የገና በዓል ለእግዚአብሔር ስጦታ ልትሰጡ ከፈለጋችሁ፣ ኀጢአት ከሚገጣጠምበት ሰልፍ ለቃችሁ ውጡና ድጋሚ አትመለሱ። በዚያ ምትክ የፍቅር መገጣጠሚያ ሰልፍ ላይ ተሰለፉ። የንጉሡ የእግዚአብሔር ስም ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጥቶ በጻድቃን ምስጋና እና ክብር መካከል ቆሞ የሚደነቅበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ በዚህ የገና አንድነት ላይ ግብረ ዐበሮች ሁኑ።