እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። (ዕብራውያን 4፥16)
እያንዳንዳችን እርዳታ ያስፈልገናል። እኛ ፈጣሪ አይደለንም። ሊሟሉ የሚገቡ ጉድለቶች አሉን። ድክመቶች አሉብን። ግራ መጋባት ውስጥ እንገባለን። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውስንነቶች አሉን። እርዳታ ያስፈልገናል።
ከዚህም ባለፈ እያንዳንዳችን የተሸክምነው ነገር አለ፦ ኃጢአቶች አሉብን። ስለዚህም የሚያስፈልገን እርዳታ የማይገባን መሆናችንን ከውስጥ ከልባችን እናውቃለን። በዚህም ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባን ይሰማናል።
ሕይወቴን ለመኖር፣ ሞትን ለመጋፈጥ እና ዘላለማዊነትን ለመካፈል እርዳታ እፈልጋለሁ። በቤተሰቤ፣ በትዳር ጓደኛዬ፣ በልጆቼ፣ በብቸኝነቴ፣ በሥራዬ፣ በጤንነቴ፣ በገንዘቤ ዙሪያ እርዳታ ያስፈልገኛል። የሚያግዘኝ ያስፈልገኛል። ሆኖም ግን የምፈልገው እርዳታ አይገባኝም።
ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ? ደካማ መሆኔን ክጄ፣ ምንም ዐይነት እርዳታ እንደማያስፈልገው ልዕለ-ሰው ለመሆን መጣጣር እችላለሁ። ወይም ደግሞ ሁሉንም አሽቀንጥሬ ጥዬ በኀጢአት እና በዓለማዊ ደስታ መዘፈቅ እችላለሁ። እሱም ካልሆነ ደግሞ ራሴን ለተስፋ መቁረጥ ሽባነት አሳልፌ መስጠት እችላለሁ።
ነገር ግን በዚህ ተስፋ ቢስ ሕይወት ላይ ታላቁ እግዚአብሔር ይህንን ያውጃል፦ ተስፋ መቁረጥን ተስፋ በመስጠት ድል ሊነሳ፣ የተኮፈሱትን ሊያሳፍር፣ የሚሰጥመውንም ምስኪን ነፍስ ሊታደግ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ሊቀ ካህናት ሆነ።
አዎ፣ በእርግጥ ሁላችንም እርዳታ ያስፈልገናል። ማናችንም ብንሆን የሚያስፈልገን እርዳታ አይገባንም። ነገር ግን ለተስፋ መቁረጥ፣ ለኩራትና ለልቅነት እጅ አንሰጥም። እግዚአብሔር የሚለውን ተመልከቱ። ታላቅ ሊቀ ካህን ስላለን፣ የእግዚአብሔር ዙፋን ለእኛ የጸጋ ዙፋን ነው። ከዚያ የጸጋ ዙፋን በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እና ምሕረትን እናገኛለን። የሚረዳንን ጸጋ! ተገብቶን የሚሰጠን እርዳታ ሳይሆን ቸር እርዳታ ነው። ለዚህም ነው ሊቀ ካህኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው።
ያላችሁት መፈናፈኛ የሌለው ሁኔታ ውስጥ አይደለም። ለዚያ ውሸት እጅ አትስጡ። እርዳታ ያስፈልገናል። እርዳታው አይገባንም። ነገር ግን፣ እንወስደው ዘንድ ተዘጋጅቶልናል። ሊቀ ካህናችሁን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስን ብትቀበሉ፣ በእርሱ ብታምኑና በእርሱም አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር ብትቀርቡ፣ እርዳታው አሁን እና ለዘላለም ሊኖራችሁ ይችላል።