ቤቶቹ ነን | ሕዳር 4

ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቶአል፤ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር፤ ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን። (ዕብራውያን 3፥​3–6)

በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመኩና ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤት ናቸው። ይህም ኢየሱስ ፈጣሪያችን፣ ባለቤታችን፣ ገዢያችን እና ረድኤታችን የሆነው ጥንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ጭምር መሆኑን ያሳያል።

ኢየሱስ የዚህ ቤት “ቤት ሠሪ” ተብሎ ተጠርቷል። ሙሴ ቤት ሠሪ አልነበረም። የቤቱ አካል ነበር። ስለዚህ፣ “ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቶአል” ይላል። ስለዚህ ሙሴ ቤቱን በመምራት እና የእግዚአብሔርን ቃል ለቤቱ በመስጠት ታላቅ ቢሆንም፣ የቤቱ አንድ አካል ብቻ ነበር። ኢየሱስ ግን ቤቱን ሠራ። ስለዚህ በኢየሱስ የምንመካና ተስፋ የምናደርግ ከሆነ እኛ ቤት ነን፤ ኢየሱስም አናጢያችን፣ ባለቤታችን፣ ገዢያችን እና ረድኤታችን ነው። ቤቱ እንዲወድም ወይም እንዲፈርስ አይፈቅድም።

ጸሐፊው ከዚህ በማስከተል ምሳሌውን ከቤት እና ከቤት ሠሪ ወደ ልጅ እና አገልጋይ ይለውጠዋል። “ሙሴ… በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር፤ ክርስቶስ ግን… እንደ ታማኝ ልጅ ነው” ይለናል። ስለዚህ ክርስቶስ የቤቱ አንድ አካል ሆነ ማለት ነው። የቤተሰቡ አንድ አካል ሆነ። ይህም ሆኖ ክብሩ እጅግ ከሙሴ የበለጠ ነው። ሙሴ አገልጋይ ነበር። ክርስቶስ ልጅ ነው፤ ወራሽ ነው።

እኛ ደግሞ የዚህ ቤተሰብ አካል ነን። ዕብራውያን 3፥6 “እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን” ይላል። በርግጥ ለሙሴ የሚገባውን ቦታ እና ዕውቅና አንነፍግም። የዕብራውያን መጽሐፍ ዋናው መልእክት ግን ክርስቶስ ከሁሉ ይልቃል የሚል ነው። በሁሉም መንገድ የላቀ ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቤት “ቤተ ሠሪ” ነው። በእግዚአብሔር ሕዝብ ቤት ውስጥ ልጅ ነው። ሙሴን ልናከብረው ይገባል። ሠሪያችን እና ወንድማችን የሆነውን ኢየሱስን ግን እናመልከው።