“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና (ዮሐንስ 15፥5)።”
እስቲ ከመናገር ውጭ ሌላ ምንም ማድረግ የማትችሉ ሽባ (ፓራላይዝድ) ሰው እንደሆናችሁ አስቡ። እንበልና፣ አንድ ጠንካራ እና ታማኝ ጓደኛችሁ ከእናንተ ጋር ሊኖር፣ በሚያስፈልጋችሁ ሁሉ ሊረዳቹ ቃል ይገባል። ሊጠይቋችሁ በሚመጡ ሰዎች ፊት ይህንን ወዳጃችሁን እንዴት አድርጋችሁ ታሞግሳላችሁ?
ከአልጋችሁ ተነሥታችሁ እርሱን በመሸከም ነው ለውለታው ምሥጋናችሁን የምትገልጹለት? አይደለም! እንዲያውም “ና እስቲ ቀና አድርገኝ እባክህ፤ እንግዳው እንዲታየኝ ትራሱን ከጀርባዬ አድርግልኝ፣ መነጽሬን አስተካክልልኝ፣ ዐይኔ ላይ አድርግልኝ” ነው ምትሉት።
በዚህም እንግዳው ከተማጽኗችሁ የተነሣ ጓደኛችሁ ላይ ጥገኛ እንደሆናችሁ እና ምን ያህል ጠንካራና ሩኅሩኅ እንደሆነ ይረዳል። ወዳጃችሁን የምታሞግሱት እርሱ ላይ ጥገኛ በመሆን፣ እንዲረዳችሁ በመማጸን እና በእርሱ ላይ በመደገፍ ነው።
በዮሐንስ 15፥5 ኢየሱስ፣ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ይላል። በርግጥም ሽባ ነን። ያለ ክርስቶስ፣ ክርስቶስን የሚያከብር ነገር ማድረግ አንችልም። ጳውሎስም እንደተናገረው፦ “በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ” ይለናል (ሮሜ 7፥18)።
ነገር ግን በዮሐንስ 15፥5 እንደተጠቀሰው እግዚአብሔር ክርስቶስን የሚያከብር ስራ እንድንሰራ፣ ማለትም ፍሬ እንድናፈራ ይፈልጋል። “ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል” ይላል። ልክ እንደ ጠንካራው እና ታማኙ ወዳጃችን፣ “ወዳጆች ብያችኋለሁ” (ዮሐንስ 15፥15) ያለን ኢየሱስ፣ በራሳችን ማድረግ የማንችለውን በእኛ እና ለኛ ሊያደርግልን ቃል ገብቶልናል።
ታዲያ እንዴት እናሞግሰው? እንዴትስ እናክብረው? ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልሱን በዮሐንስ 15፥7 ላይ ይሰጣል፦ “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም።” ስለዚህ፣ እንጸልይ! በክርስቶስ ፍሬ እንድናፈራ እግዚአብሔርን እንለምነው።
ዮሐንስ 15፥8 ለጥያቄያችን መልሱን ይነግረናል፦ “ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ፣ በዚህ አባቴ ይከብራል።” ታዲያ እግዚአብሔር በጸሎት እንዴት ይከብራል? ጸሎት እኛ ያለ ክርስቶስ ምንም ማድረግ እንደማንችል የምናሳይበት መንገድ ነው። ራሳችን ላይ ከማተኮር ዞር ብለን በእግዚአብሔር እርዳታ እንደምንታመን ማሳያ መንገድም ነው።