“እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁ፣ በእናንተም ዘንድ ታምራትን የሚሠራው ሕግን ስለ ጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን ስላመናችሁ?” (ገላትያ 3፥5)
ክርስቲያኖች ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር፣ “እናንተ ግን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ፣ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ናችሁ። ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፣ እርሱ የክርስቶስ አይደለም” (ሮሜ 8፥9)። መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እናንተ የመጣው በክርስቶስ ደም የተገኘውን የእግዚአብሔርን ተስፋ ስታምኑ ነው። በዚሁ እምነት አማካይነትም መንፈስ ቅዱስ ወደ እናንተ መምጣቱንና በእናንተ መሥራቱን ቀጥሏል።
ጳውሎስም በገላትያ 3፥5 ላይ፣ “እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁ፣ በእናንተም ዘንድ ታምራትን የሚሠራው ሕግን ስለ ጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን ስላመናችሁ?” በማለት ይጠይቃል፤ ምላሹም “የሰማችሁትን በማመናችሁ” የሚል ነው። ስለዚህም የመንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እኛ መምጣትና በቋሚነት ለእኛ መሰጠት የሆነው በእምነት አማካይነት ነው። እርሱ በእኛ ውስጥ ሆኖ በእኛ እማካይነት የሚያከናውነው ሁሉ በእምነት ነው።
እንደ እኔ ከሆናችሁ፣ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችሁ በኃይል እንዲሠራ ጠንካራ ፍላጎት ይኖራችሁ ይሆናል። ምናልባትም መንፈሱን በእናንተ፣ በቤተ ሰባችሁ ወይም በቤተ ክርስቲያናችሁ ወይም በከተማችሁ ላይ እንዲያፈስ እግዚአብሔርን በለቅሶ ለምናችሁት ሊሆን ይችላል። እንደዚህ አይነት ልመናዎች ትክክለኛና መልካም ልመናዎች ናቸው። “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!” (ሉቃስ 11፥13)።
ነገር ግን ራሴን በተደጋጋሚ የማገኘው የእግዚአብሔርን ተስፋ ማመን ሲሳነኝና ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ራሴን ክፍት ማድረግ ሲያቅተኝ ነው። ይህን ስል መንፈስ ቅዱስን ስንጠይቀው ይመጣል የሚለውን ተስፋ ብቻ ማመልከቴ አይደለም። ሌሎች ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቀጥታ ያልተያያዙትን የከበሩ ተስፋዎችን ሁሉ ማለቴ ነው፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ለእኔ ሕይወት ያለውን አቅርቦት። ለምሳሌ፦ “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል” የሚለውን ቃል ኪዳን ማመን ይከብደኛል (ፊልጵስዩስ 4፥19)። የእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰጠን ቀጣይነት ባለውና ኃይለኛ በሆነ መንገድ ነው፤ ይኸውም ለተወሰኑ ሁኔታዎች በተሰጡ ተስፋዎች ላይ ባለ እምነታችን አማካይነት ይሰጠናል። የሰጠኝን ተስፋ እንደሚፈጽመው አሁን ላይ በእርግጥ በእርሱ እታመናለሁ?
የመንፈስ ቅዱስን ኃይል በሕይወታቸው የሚፈልጉ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ተሞክሮ ውስጥ የጠፋው ይሄ ነገር ነው። “መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን የሰማነውን በማመን ነው” (ገላትያ 3፥5)። ይህም ስለ መንፈስ ቅዱስ የተገባልንን አንድ ወይም ሁለት ተስፋዎችን ማመን ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የነፍስን ፍላጎት ሁሉ የሚያረካው የእግዚአብሔር ሕልውና ለእኛ የሚያደርግልንን ነገር ሁሉ ማመንን ያካትታል።