ለሚያስደስቱን ነገሮች የተለይ ቦታ እንሰጣቸዋለን | ጥቅምት 30

እግሮችህ ሰንበትን እንዳይሽሩ ብታሳርፍ፣ በተቀደሰው ቀኔ የልብህን ባታደርግ፣ ሰንበትን ደስታ፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቀን የተከበረ ብለህ ብትጠራው፣ በገዛ መንገድህ ከመሄድ፣ እንደ ፈቃድህ ከማድረግና ከከንቱ ንግግር ብትቈጠብ፣ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በምድር ከፍታዎች ላይ እንድትጋልብ፣ የአባትህን የያዕቆብን ርስት ጠግበህ እንድትበላ አደርግሃለሁ” (ኢሳይያስ 58፥​13–14)

እግዚአብሔርን ሳናከብር እግዚአብሔርን መፈለግ ይቻላል። ፍለጋችን እግዚአብሔርን እንዲያከብር የምንሻ ከሆነ፣ ከእርሱ ጋር ካለ ሕብረት የተነሣ ለሚገኘው ደስታ ስንል፣ እርሱን መፈለግ አለብን።

ሰንበትን ለዚህ ምሳሌ ተመልከቱ። እግዚአብሔር በተቀደሰው ቀኑ የራሳቸውን ተድላ በመፈለጋቸው ህዝቡን ይገስጻል። “እግሮችህ ሰንበትን እንዳይሽሩ ብታሳርፍ፣ በተቀደሰው ቀኔ የልብህን ባታደርግ” ይላል። ምን ማለቱ ነው? ደስታችንን በጌታ ቀን መፈለግ የለብንም ማለቱ ነው? አይደለም፣ ምክንያቱም ቀጥሎ ያለው “ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቀን የተከበረ (ደስ የሚያሰኝ) ብለህ ብትጠራው” ስለሚል ነው። በቁጥር 14 ላይ ደግሞ፦ “በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል” ይላል። ስለዚህ እርሱ እየተቸው ያለው ነገር በሰንበት ቀን በአምላካቸው ውበት፣ ይህ ቀን በሚወክለው ዕረፍትና ቅድስና ከመደሰት ይልቅ በራሳቸው ትርኪምርኪ ደስተኛ መሆናቸውን ነው።

የሚያስደስት ነገር መፈለጋቸውን እየወቀሰ አይደለም። ወቀሳው የፍላጎታቸውን ድክመት ወይም ርካሽነት ላይ ነው። ሲኤስ ሉዊስ፦ “በጣም በቀላሉ ወይም በትንሽ ነገር የምንደሰት ነን” ብሏል። በዓለም ነገሮች ረክተው ተቀምጠዋል፤ እነዚህንም ነገሮች ከጌታ በላይ ያከብሯቸዋል።

ሰንበትን “ደስታ” ብሎ መጥራት፣ የጌታን ቅዱስ ቀን “ክቡር” ብሎ ከመጥራት ጋር ትይዩ መሆኑን አስተውሉ። “ሰንበትን ደስታ፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቀን፣ የተከበረ ብለህ ብትጠራው” በማለት ተናግሯል። ይህ ማለት በቀላሉ፣ የምትደሰትበትን ነገር ታከብራለህ፣ ወይም የሚያስደስትህን ነገር ከፍ ከፍ ታደርገዋለህ ማለት ነው።

በእግዚአብሔር መደሰት እና እግዚአብሔርን ማክበር አንድ ናቸው። የእርሱ ዘላለማዊ ዓላማ እና የእኛ ዘላለማዊ ደስታ በአንድ የአምልኮ ልምምድ ውስጥ ተናብረዋል። የጌታ ቀን የሚያመለክተው ይህን ነው። በእርግጥ፤ ህይወት ሁሉ የሚያመለክተው ይህን ነው።